ህክምናቸውን አቋርጠው የወጡ የኢቦላ ታማሚዎች ሞቱ

የአለምጤና ድርጅት ነርሶች ክትባቱን ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በህክምና ተቋም የሚገኙ የኢቦላ ታማሚዎችን ቤተሰቦቻቸው ወደ ቤተክርስቲያን ሊወስዷቸው በመፈለጋቸው ምክንያት ህክምናውን አቋርጠው እንደወጡ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የአለም ጤና ድርጅት ባለሙያ የሆኑት ኢውጌኔ ካባምቢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የታማሚዎቹ ዘመዶች በድንበር የለሽ ሃኪሞች ድርጅት በሚመራው ማዕከል በመምጣት ለፀሎት ሊወስዷቸው እንደሚፈልጉ ገልፀውላቸዋል።

በቦታው የሚገኙ ባለሙያዎች ህክምናቸውን እንዲቀጥሉ ሊያሳምኗቸው ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።

በኋላም በሞተር ሳይክል እንደተወሰዱ ገልፀዋል። እነርሱን ለመፈለግ የፖሊስ ትዕዛዝም ወጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ህክምናውን ጥለው ከወጡ ታማሚዎች አንዱ ቤቱ ከደረሰ በኋላ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን በጥንቃቄ መቅበር ይቻል ዘንድም አስከሬኑ ወደ ህክምና ተቋሙ ተመልሷል።

አንደኛው ምባንዳካ ከተማ ወደሚገኝ የህክምና ቦታ የተመለሰ ሲሆን ህክምናቸውን ትተው ከሄዱት ሶስት ታማሚዎች መካከል ሁለቱ ሞተዋል።

"እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች መፈጠራቸው ለጤና ባለሙያዎቹ አዲስ ተግዳሮት ሆኗቸዋል። የዚህን ተላላፊ በሽታ ስርጭት ለመግታትም ፈታኝ ያደርገዋል።" ብለዋል።

ኢቦላ መድሃኒት የሌለው በሽታ ሲሆን፤ አንድ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ በሚኖርባት ምባንዳካ ቫይረሱ በፍጥነት ሊዛመት ይችላል ሲሉ የጤና ባለሙያዎቹ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በመሆኑም ተነጥሎ ለብቻ በተዘጋጀ ቦታ ክትትሉን ማድረግ ስርጭቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዋነኛው መንገድ እንደሆነም ተገልጿል።

"ህክምናውን አስገድዶ መስጠት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መፍትሄ አይሆንም" ያሉት ባለሙያው "ታማሚውን መከታተል ግን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው" ይላሉ።

በመሆኑም ህክምናቸውን አቋርጠው የወጡት ሶስቱ ታማሚዎች ቤተሰቦች ላይ ክትትል እየተደረገ ሲሆን የተወሰኑት ክትባቱን ተከትበዋል።

የአለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ኢቦላ ዳግም ካገረሸ በኋላ አምሳ ስምንት ኬዞች ተመዝግበዋል።

ከእነዚህ መካከል ሃያ ሰባቱ የሞቱ ሲሆን ከሟቾቹ የሶስቱ በኢቦላ ምክንያት እንደሆነ ተረጋግጧል።