ለረጅም ሰዓት ስክሪንን መጠቀም ለካንሰርና ለልብ ህመም ይዳርጋል

Man watching tablet on sofa Image copyright Getty Images

ረጅም ሰዓት ስክሪን ላይ እየተመለከቱ መቆየት ከካንሰርና ከልብ ህመም ግንኙነት እንዳለው አዲስ የወጣ ጥናት አመለከተ።

የግላስኮው ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንዳሉት በትርፍ ሰዓታቸው ሳይቀር በቴሌቪዥንና በኮምፒዩተር ስክሪኖች ላይ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ 39 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን መረጃ ተንትኗል።

በጥናቱ መሰረትም በስክሪኖች ላይ ረጅም ሰዓት የሚያጠፉ ሰዎች አነስተኛ ቆይታ ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነፃፀር የጤና ሁኔታቸው በእጥፍ የተዳከመ ሆኖ አግኝተውታል።

ከጥናቱ መሪዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃሰን ጊል እንዳሉት የጥናቱ ግኝት የህብረተሰብ ጤና መመሪያ ላይ ለውጥን ሊያስከትል ይችላል፤ ለልብ ህመም ሲዳርግ ሞትንም ያፋጥናል ብለዋል።

"የየሰዉ ረጅም ሰዓት የመቀመጥ ልማድ ሊለያይ ይችላል፤ ነገር ግን ከስክሪን ላይ የምናሳልፈው ጊዜ ከመጠን ያለፈ ከሆነ በአጠቃላይ ጤናን እንደሚጎዳ አመላክቷል ብለዋል።

የሰውነት አቋም፣ ጥንካሬና የሰውነት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

የጥናቱ ውጤትም ለተጠቀሱት የጤና እክሎች ከሚዳርጉ ሌሎች ምክንያቶች ማለትም ሲጋራ ማጨስ፣ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲሁም ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ነፃ ሆኖ የተካሄደ ነው ።

የጥናቱ ፀሃፊ ዶክተር ካርሎስ በበኩላቸው "ዝቅተኛ የሰውነት አቅም፣ ጥንካሬ፣ የሰውነት አቋምና የሰውነት እንቅስቃሴ ያላቸው ሰዎች ረጅም ሰዓት የመቀመጥ ልምዳቸውን በመቀነስ ቀድመው ሊከላከሉት ይችላሉ'' ሲሉ መክረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

ተያያዥነት ያላቸው የኢንተርኔት ማስፈንጠሪዎች

ቢቢሲ ለሌሎች የኢንተርኔት ገጾች ኃላፊነት አይወስድም