የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነችው በሂደት ነው

የወባ ትንኝ Image copyright Science Photo Library

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በዓመት ከ 200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ይያዛሉ።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 በወባ ከተያዙ ሰዎች መሀከል ግማሽ ሚሊዮኑ ህይወታቸው አልፏል። ከሟቾቹ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።

የወባ ትንኝ ሁሌም አደገኛ ነፍሳት አልነበረም። የወባ ትንኝ የአደገኛነት መጠን አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰው በአዝጋሚ ሂደት መሆኑን ያውቁ ኖሯል?

ካምብሪጅ ውስጥ የሚገኘው ዌልካም ሳንገር ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት የወባ ትንኝ የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ነፍሳት ለመሆን ያለፈበትን የእድገት ደረጃዎችን ያሳያል።

ጥናቱ የተሰራው ሰባት የወባ ትንኝ ዝርያዎችን በናሙናነት በመውሰድ ሲሆን ከ50 ሺህ ዓመታት በፊት ትንኙ አንድ አይነት ዝርያ ብቻ እንደነበረው ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል።

በጥናቱ መሰረት የትንኝ ዝርያው ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎችን ወደሚያጠቃ አደገኛ ነፍሳትነት ተሸጋግሯል።

ከተመራማሪዎቹ አንዱ ዶ/ር ማት በርማን እንደሚለው ትንኞች ከጊዜ በኋላ ያሳዩት የዘረ መል ለውጥ የሰዎችን ቀይ የደም ህዋስ ማጥቃት የሚችሉበት ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል።

"ጥናታችን ጥገኛ ህዋሳት ሰውነት ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚቆዩበትን እንዲሁም እየተከፈሉ በመባዛት ሰውነት ውስጥ በወባ ትንኝ የሚሰራጩበትን ሂደት ይዳስሳል" ሲል ያስረዳል።

ከጥገኛ ህዋሳቱ መሀከል ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም የተባለው ከፍተኛ የጤና እክልን ያስከትላል። ለህልፈት የምትዳርገው ሴት የወባ ትንኝ ሰዎችን ስትነድፍ የቺምፓንዚና ጎሬላ ዝርያዎችን የሚያጠቁ ነፍሳትም አሉ።

አጥኚዎቹ ጋቦን ወደሚገኝ የጦጣ ማቆያ አቅንተው ከእንስሳቱ የደም ናሙና ወስደዋል። "ጤነኛ በሆኑት እንስሳት ደም ውስጥ ጥገኛ ህዋሳት ተገኝቷል" ሲል ዶክተሩ ይናገራል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት የደም ናሙናዎቹ የወባ ትንኝን ዘረ መል ለማወቅና በዝግመተ ለውጥ ያሳዩትን ለውጥ ለመገንንዘብ ችለዋል። የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነበትን ሂደትም ደርሰውበታል።

በጥናቱ ከተካተቱት ሰባት የወባ ትንኝ አይነቶች ሦስቱ ቺምፓንዚን፣ ሦስቱ ደግሞ ጎሬላ የሚያጠቁ ናቸው።

ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም የሚባለው አደገኛ የትንኝ ዝርያ ከ 50 ሺህ ዓመታት በፊት ቢገኝም የሰው ልጆችን ወደማጥቃት የተሸጋገረው ከ 3,000 እና ከ 4,000 ዓመት በፊት ነው።

"የወባ ትንኝ ሰዎችን ወደሚያጠቃ ነፍሳትነት ለማደጉ የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ምክንያት ነው" ሲል ዶ/ር ማት ያስረዳል።

የሊቨርፑሉ ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜዲሲን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጃኔት ሄሚንግዌይ "የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነበትን ጊዜና ሁኔታ ስለሚያሳይ ጠቃሚ ነው" ትላለች።

የትንኙ አደገኛ የሆነበትን ሂደት መገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ተናግራለች።

"ብዙ ሰዎች ወባ ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላለፍ መሆኑን አያውቁም። የሰው ሰውነትን ተዋህደው ወደ አደገኛነት የተሸጋገሩትም በጊዜ ሂደት ነው" ስትል ትገልጻለች።