ራስዎን ካላስፈላጊ የስልክ ጥሪ እንዴት ይታደጋሉ?

አንድ ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኩ ተደውሎለት ለማንሳት ሲዘጋጅ
የምስሉ መግለጫ,

የማይስፈልግ የስልክ ጥሪ ሊደርስዎት ይችላል

እኩለ ለሊት ላይ ነው። ከኃይለኛ እንቅልፍ የስልክዎ ጩኸት ይቀሰቅስዎታል። ስልክዎን ሲመልሱ በሌላኛው የስልኩ ጫፍ ምላሽ የሚሰጥዎ ሰው ባይኖርስ?

'ሄሎ' በሚል ሰው ፈንታ የህክምና ኢንሹራንስ ይፈልጉ እንደሆነ የሮቦት ድምጽ ቢጠይቅዎስ? ከጣፋጭ እንቅልፍዎ የተነሱት ያለምንም ምክንያት በመሆኑ ይበሳጫሉ።

ተመሳሳይ ሁነት ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ሊገጥም ይችላል። ነገሩ ወዲህ ነው። በስልክ የሚሰማው ድምጽ የማሽን ሲሆን 'ሮቦኮልስ' በመባል ይታወቃል።

በስልክ የሚተላለፈው ድምጽ ከጥሪው በፊት የተቀዳ የማሽን አልያም የሮቦት ድምጽ ነው።

የስልክ ጥሪውን በህጋዊ መንገድ የሚጠቀሙበት ቢኖሩም ባልተገባ ሁኔታ ለንግድ የሚያውሉትም አልታጡም።

ለአብነት አሜሪካና ካናዳን ብንወስድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ይጠቀሙበታል። አየር መንገዶችም ማስታወቂያ ለመንገር ይገለገሉበታል።

ባለፈው ሚያዝያ አሜሪካ ውስጥ 3,400 ሚሊየን የሮቦኮል ጥሪዎች ለ 324 ሚሊዮን ሰዎች መድረሳቸውን የካሊፎርኒያው ዩሜል ድርጅት አሳውቋል።

በዋነኛነት ጥሪውን የሚያደርጉት የህክምና እና የመኪና ኢንሹራንስ ድርጅቶች እንዲሁም የቤት ደላላዎችና ሥራ አፈላላጊዎች ናቸው።

እነዚህ ድርጅቶች ለሰዎች የሚደውሉት በዘፈቀደ ነው። ለአንድ ግለሰብ በቀን ወይም በሳምንት ውስጥ በርካታ ጊዜ ሊደውሉ ይችላሉ። አንዳንድ ድርጅቶች በደቂቃ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠር ጥሪ ማድረግ ይችላሉ።

የምስሉ መግለጫ,

ሮቦኮል እንደሀሰተኛ ኢሜል ነው

ፌደራል ትሬድ ኮሚሽን የተሰኘው ድርጅት እንደሚያመለክተው የስልክ ጥሪው ሲደረግ የደዋዩ ቁጥር ሊደበቅ ወይም የተሳሳተ ቁጥር ሊወጣ ይችላል። ትክክለኛ የስልክ ቁጥር በመጠቀምም ጥሪው የሚተላለፍበት አጋጣሚ አለ።

ባለፈው ዓመት በአንድ ወር ውስጥ 375 ሺህ ሰዎች ስለስልክ ጥሪዎቹ ቅሬታ አቅርበዋል።

ድርጅቱ እንደሚለው የስልክ ጥሪዎቹ ሲደረጉ ደዋዮቹ ያሉበትን ቦታ መደበቅ የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ስለሚጠቀሙ ከየት እንደተደወለ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

እነዚህ ጥሪዎች ሲደርዎ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ያውቃሉ?

መሰል ጥሪ ሲደርስዎት መጀመሪያ ማድረግ ያለብዎት ስልኩን በፍጥነት መዝጋት ነው። በስልክዎ ላይ ቁጥር እንዲያስገቡ ቢጠየቁም አያስገቡ። ቁጥር አስገቡ ማለት ራስዎን ለተጨማሪ ስልክ ጥሪዎች አጋለጡ ማለት ነው።

አስከትለው የስልክዎን ሲም ለገዙበት ድርጅት ስለሁኔታው ያሳውቁ። ደዋዩን ወደ ስልክዎ እንዳይደውል ማድረግ ይችላሉ። ቲሎውስ ወይም ሁኮልስ የተባሉ ድረ ገጾች መሰል ጥሪዎችን ለማመልከት የተዘጋጁ ስለሆኑ መጠቀም ይችላሉ።

የቴክኖሎጂ መረጃዎች የሚሰራጩበት ዘ ቨርጅ የተባለው የዩቲዩብ ገጽ አርታኢ የሆነው ክሪስ ዌልች "በየቀኑ ስድስት የተሳሳቱ ጥሪዎች ይደርሱኛል" ይላል።

ከጥሪዎቹ መሀከል ትርጉም አልባ የሆኑ ማስፈራሪያዎች ይገኙበታል። "ግብር ካልከፈሉ ይታሰራሉ" የሚል መልዕክትን እንደምሳሌ የሚጠቅሰው ክሪስ "መልዕክቶቹ በጣም ይረብሻሉ" ይላል።

ክሪስ እንደመፍትሄ የሚያስቀመወጠው ስልክ ቁጥሩን መዝግቦ ሲደውል እንዳይታይ ማገድ (ብሎክ ማድረግ) ነው። ሮቦኮል የሚያደርገውን ስልክ ቁጥር ማመልከትም ይቻላል።

የምስሉ መግለጫ,

የማይፈልጉት ጥሪ ከሆነ ስልኩን ይዝጉት

ጥሪ ለማገድ የሚያስችል መተግበሪያ ያላቸው የስልክ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ። አግልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብም ይቻላል።

ሮቦኮል የሚያስቸግራቸው ሰዎች የተለያዩ መተግበሪያዎችን መጫንም ይችላሉ። ዩሜል፣ ሮቦኪለር፣ ትሩኮለር ወይም ሂያ የተባሉ መተግበሪያዎችን ክሪስ ይጠቅሳል።

ክሪስ እንደሚናገረው ስልክ ሲገዛ ሮቦኮል ማገድ የሚችል መተግበሪያ አላቸው። ለአብነት ያህል የሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ እና ኖት ስልኮች የሮቦኮል ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ።

የስልክ ቀፎ ላይ ከተመዘገቡ ቁጥሮች ውጪ ሲደውሉ ተጠቃሚው እንዳያይ የሚያስችሉ መንገዶች አሉ። 'ዱ ኖት ዲስተርብ' የሚል ቁልፍ ስልክ ላይ በመጫን የማይፈለጉ ጥሪዎችን መከላከል ይቻላል።

የአንድሮይድና አይፎን ስልኮች ከተመዘገቡ ስልኮች ውጪ ጥሪ ያለመቀብ አማራጭ ይሰጣሉ።

ክሪስ እንደሚለው አንድ ሰው የሚፈልጋቸውን ስልኮች እስከመዘገበ ድረስ ባልተፈለጉ ጥሪዎች እንዳይረበሽ ማድገግ የተሻለ አማራጭ ነው።