ኬንያዊያን ፍየል አርቢ ቤተሰቦች የአውሮፓ ህብረትን ሊከሱ ነው

የአውሮፓ ህብረትን የከሰሱት ቤተሰቦች Image copyright TWITTER/FRIENDS OF THE EARTH

ፍየል በማርባት የሚተዳደሩ ኬንያውያን ቤተሰቦች የአውሮፓ ሕብረትን ፍርድቤት ሊያቆሙ ነው።

ቤተሰቦቹ ሕብረቱን የከሰሱት ከአየር ንብረት መዛባት ሊጠብቃቸው ባለመቻሉ ቤታቸውና መተዳደሪያ ንብረቶቻቸው ላይ አደጋ በመጋረጡ እንደሆነ ገልፀዋል።

በሰሜን ኬንያ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩት የጉዩ ቤተሰቦች ከበርካታ ከሳሾች መካከል አንዱ ናቸው።

ጉዩ ለኤ ኤፍ ፒ እንደተናገሩት የአካባቢያቸው ሙቀት በጣም ከፍተኛና ተደጋጋሚ በመሆኑ ለአምስት ልጆቻቸው ጤናና የትምህርት ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

"በአካባቢያችን ከፍተኛ ሙቀትን እያስተናገድን ነው፤ ይህም ህይወታችንን በተለያየ መልኩ እየተፈታተነው ነው" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

"የምንጠጣውም ሆነ ለከብቶቻችን የሚሆን ውሃ እየጠፋ ነው፤ በተለይ የልጆቼ ጤና አደጋ ላይ ነው" ሲሉም ይገልፃሉ።

በአካባቢው ያለው የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ይሆናል ያሉት እኝህ አባት ፤ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ትምህርታቸውን ለመከታተል ከባድ ሆኖባቸዋል ይላሉ።

የከሳሾቹ ቡድን 10 ቤተሰቦችን የያዘ ሲሆን ከፈረንሳይ የመጡ የወይን አምራች ገበሬዎችን እንዲሁም በሳሚ ማህበረሰብ የደጋ አጋዘንን የሚጠብቁ አርብቶ አደሮችን ይጨምራል።

የአውሮፓ ህብረት በአውሮፓውያኑ 2030 በአገር ውስጥ ያለውን የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀት 40 በመቶ ለመቀነስ የገባው ቃል መሰረታዊ መብቶቻችንን ሊያስጠብቅልን አልቻለም የሚል ቅሬታ አላቸው።