የደቡብ አፍሪካው መሪ ራማፎሳ የደመወዛቸውን ግማሽ ለማንዴላ በጎ አድራጎት ድርጅት ሰጡ

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲይሪል እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ከእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስተር ቴሬዛ ሜይ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት መንገዶችን ለመቀነስ መግለጫ ሰጥተዋል።
የምስሉ መግለጫ,

ሲሪል ራማፎዛ በንግድ ዘርፍ የታወቁ ናቸው

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ የደመወዛቸውን ግማሽ ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚለግሱ አስታውቀዋል።

ፕሬዚደንቱ ይህንን ያደረጉበት ዋና ዓላማ ሌሎች በአገሪቷ ያሉ ባለሃብቶችም የተወሰነ ገንዘባቸውን አገሪቱን ለመደገፍ እንዲያውሉ ለማበረታት ነው።

የሚያደርጉት የ1.8 ሚሊዮን የደቡብ አፍሪካ ራንድ ወይም 130 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ በኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን አስተዳደር ስር ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ጠቅላላ ሃብታቸው 450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ የናጠጡ ሃብታም ወንዶች መካከል አንዱ ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ 2012 በ2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጎሽ ከነ ግልገሏ ለመግዛት ተጫርተው የነበሩት ራማፎሳ ለድሆች ግድ የላቸውም የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል።

የ65 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ራማፎሳ እንደ አውሮፓውያኑ 2012 ምክትል ፕሬዚደንት ከመሆናቸው አስቀድሞም የንግድ ሰው ነበሩ።

በቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ፣ በሚዲያ እንዲሁም በመጠጥና ፈጣን ምግቦች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የግል ድርሻ አላቸው።

በደቡብ አፍሪካ ባለቤትነቱ የአሜሪካ የሆነው የማክዶናልድ ንግድ ባለቤትም ናቸው።

የፕሬዚደንቱ ውሳኔ በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ የተዘበራረቀ ስሜትን ፈጥሯል። አንዳንዶች "ድጋፉ ኢምንት ነው" ሲሉ ሌሎች ደግሞ "ከራስ ወዳድነት የራቀ ውሳኔ ነው፤ ይህም በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ዘንድ በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የመሳተፍ ባህልን ያሳየ እንቅስቃሴ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም ለኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን ድጋፍ ለማድረግ የወሰኑት ለመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካው ዲሞክራሲያዊ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ክብር ሲሉ ተደምጠዋል።

"በግልና በማህበረሰብ ተነሳሽነት የተመሰረተ ድርጅት እንደመሆኑ ሌሎች ይህን ማድረግ የምትችሉ ባለሃብቶችም ትንንሽ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ አገር እንገባ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፉ የኔልሰን ማንዴላ መቶኛ ዓመት የልደት ቀን እለት በይፋዊ ስነስርአት ይገለፃል ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በሙስና ተጠርጥረው ስልጣናቸውን በግድ እንዲለቁ ከተደረጉ በኋላ ፕሬዚደንት ራማፎሳ ሐላፊነቱን መረከባቸው ይታወሳል።

ሌሎች መሪዎችስ ምን ሰሩ?

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዓመታዊ ደመወዛቸው 400 ሺህ ዶላር የሚሆነውን ለተለያዩ ፕሮግራሞች ድጋፍ አበርክተዋል።

የላይቤሪያው ጆርጂ ዊህ ከ100 ሺህ ዶላር ዓመታዊ ደመወዛቸው 25 በመቶ የሚሆነውን ለልማት ያውላሉ።

የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ የደመወዛቸውን 50 በመቶ አበርክተዋል።

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እንደ አውሮፓውያኑ 2015 በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማረጋጋት ከደመወዛቸው 10 በመቶ የሚሆነውን ለዚሁ ተግባር አውለዋል።