ትራምፕ የሰረዙት ውይይት ሊደረግ እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ

ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን

ከሰሜን ኮሪያው ኪም ጁን ኡን ጋር ለማድረግ ያቀዱትን ውይይት የሰረዙት ዶናልድ ትራምፕ ውይይቱ አሁንም በተያዘለት ቀጠሮ ሊደረግ እንደሚችል ተናገሩ።

ትራምፕ ለዘጋቢዎች "የሚሆነውን እናያለን። (ውይይቱ) በሰኔ 12/2018 እኤአ ሊደረግ ይችላል። አሁን በሰሜን ኮሪያ በኩል ካሉ ወገኖች ጋር እተነጋገርን ነው። ለመነጋገር በጣም ፈልገዋል። እኝም ውይይቱን ልናደርግ እንፈልጋለን'' ብለዋል።

በሳለፍነው ሐሙስ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ሊያደረጉት የነበረውን ውይይት መሰረዛቸውን አስታውቀው ለውሳኔያቸው የሰሜን ኮሪያን "ግልፅ የጠላትነት መንፈስ" በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ሰሜን ኮሪያ ግን በምላሹ በየትኛውም ሰዓት እና በማናቸውም ቦታ ለንግግር ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።

የሰሜን ኮሪያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪም ጊየ ግዋን የትራምፕን የቀደመ ውሳኔ ''በእጅጉ የሚያስቆጭ'' ሲሉ ገልፀውታል።

ሰኔ 12/ 2018 እኤአ በሲንጋፑር ሊደረግ የታሰበው የሁለቱ ሀገራት ንግግር ከተሳካ አንድ በመንበረ-ስልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ከሰሜን ኮሪያ መሪ ጋር ሲገናኝ በታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል።

አሁን እንደተሰረዘ የተነገለት ንግግር ይዘት እስከ አሁን ግልፅ አይደለም። ሆኖም ውይይቱ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ከኮሪያ ባህረ-ሰላጤ በማስወገድ እና ፍጥጫን በማርገብ ዙሪያ ሊያተኩር እንደሚችል ግምት ተሰጥቶታል።

ዶናልድ ትራምፕ የንግግሩን መሰረዝ ከመናገራቸው ከሰዓታት በፊት ሰሜን ኮሪያ በብቸኛ የኒዩክሌር መሞከሪያ ቀጠናዋ ዙሪያ ያሉ መተላለፊያ ዋሻዎችን ለማውደም የገባችውን ቃል እንደጠበቀች ማስታወቋ ይታወሳል።