ስደተኛው ከፈረንሳይ ሕዝብ አድናቆት እየጎረፈለት ነው

ስደተኛው ማማዱ ለነፍሱ ሳይሳሳ እንደ ፌንጣ ከወለል ወለል እየዘለለ ብላቴናውን ከሞት ታድጎታል Image copyright FACEBOOK
አጭር የምስል መግለጫ ስደተኛው ማማዱ ለነፍሱ ሳይሳሳ እንደ ፌንጣ ከወለል ወለል እየዘለለ ብላቴናውን ከሞት ታድጎታል

ከማሊ በስደት ወደ ፈረንሳይ እንደገባ የተነገረለት ማማዱ ጋሳማ የተባለ ወጣት በፈረንሳዊያን ዘንድ "ጀግና" በሚል እየተወደሰ ነው። ውዳሴው እየጎረፈለት ያለው አንድን እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ የነበረን ሕጻን ከሞት በመታደጉ ነው።

ብላቴናው ከ4ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ የተንጠለጠለና በሞት አፋፍ ላይ የነበረ ሲሆን ስደተኛው ማማዱ ለራሱ ነፍስ ፍጹም ሳይሳሳ እስከ 4ኛ ፎቅ ድረስ ተንጠላጥሎ ሕጻኑን መታደጉ ፈረንሳዊያንን ልባቸውን ነክቶታል።

ስደተኛው ማማዱ የሠራው ጀብድ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በእልፍ መዛመቱ የስደተኛውን ጀብዱና መልካም ሥራ በአጭር ጊዜ በመላው ፈረንሳይ እንዲናኝ አስችሎታል።

ማማዱ የሕጻኑን አሳሳቢ ሁኔታ በተመለከተ በደቂቃ ውስጥ ከባልኮኒ ባልኮኒ እንደ ፌንጣ እየዘለለ ጎረቤቶቹ ዘንድ በመድረስ የብላቴናውን ሕይወት ታድጓል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማርኮን ድርጊቱን ከተመለከቱ በኋላ ስደተኛው ማማዱን ቤተ መንግሥታቸው ድረስ ጋብዘው ስለፈጸመው መልካም ምግባር አሞግሰውታል።

የፓሪሷ ከንቲባ ወይዘሪት አኒ ሂዳልጎ በተመሳሳይ መልኩ ለ22 ዓመቱ ስደተኛ ማማዱ ምስጋና ማቅረቧን አስታውቃለች።

ድርጊቱ የተፈጸመበትን ሰፈር አስታካ ከንቲባዋ ስደተኛውን "የ18ኛ ጎዳና ስፓይደርማን" ስትል አሞካሽተዋለች።

ከንቲባዋ በትዊተር ገጽ እንደጻፈችው "ማማዱ ከማሊ ወደ ፈረንሳይ አዲስ ሕይወት ለመምራት በስደት መምጣቱን ገልጾልኛል። እኔም የመለስኩለት የፈጸምከው ጀግንነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን በመሆኑ አዲሱን ሕይወትን ለማቅናት የፓሪስ ነዋሪዎች ከጎንህ እንደሚሆኑ ነው።" ስትል የስደተኛው መጪ ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ጠቁማለች።

ይህ ትዕይትን የተፈጸመው ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ማምሻውን ነው።

ስደተኛው ማማዱ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው በ18ኛው ጎዳና ሲያልፍ ሰዎች ተሰብስበው መመልከቱንና ሕጻኑን በዚያ ሁኔታ ሲመለከት ድርጊቱን መፈጸሙን አብራርቷል።

ተያያዥ ርዕሶች