የሊቨርፑሉ በረኛ ሎሪስ ካሪየስ የግድያ ዛቻዎች እየደረሱት ነው

የሊቨርፑሉ በረኛ ሎሪስ ካሪየስ Image copyright Getty Images

የመርሲሳይድ ፖሊስ ከሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ በኋላ የሊቨርፑሉ በረኛ ሎሪስ ካሪየስ ላይ እየደረሱ ያሉ የግድያ ዛቻዎችን እየተከታተልኩ ነው አለ።

የ24 ዓመቱ ጀርመናዊ በረኛ በቅዳሜው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ በፈጸማቸው ሁለት ስህተቶች ምክንያት እሱ እና ቤተሰቦቹ ብዙ የግድያ ዛቻዎች እያስተናገዱ ነው።

ካሪየስ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በስታዲየሙ ለተገኙ የሊቨርፑል ደጋፊዎች እያለቀሰ ይቅርታ ጠይቋል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች እየደረሱበት ያሉትን ማስፈራሪያዎች እና የግድያ ዛቻዎች በጥብቅ እየተከታተለ እንደሆነ የከተማው ፖሊስ ገልጿል።

ማንኛውም ዓይነት ማስፈራሪያም ሆነ አጸያፊ አስተያየት በምርመራው ውስጥ ስለሚካተት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ይጠንቀቁ ብሏል ፖሊስ።

በተያያዘ ዜና የግብጽ እና የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሃመድ ሳላህ ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ ለራሺያው የዓለም ዋንጫ ለመጫወት ተስፋ እንዳለው ገልጿል።

ግብጻዊው በቅዳሜው የሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ወቅት ትከሻው ላይ በደረሰበት ጉዳት ከሜዳ በእንባ ነበር የወጣው።

''የናንተ ፍቅር እና ድጋፍ ብርታት ሆኖኛል። ምንም አስቸጋሪ ቢመስልም ለቀጣዩ የዓለም ዋንጫ እንደምደረስ አስባለው'' ብሏል ሳላህ በትዊተር ገጹ ላይ።

ከጨዋታው በኋላ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጉዳቱ በጣም ከባድ ነው፤ ሁኔታው ደስ አይልም ብለው ነበር።

ግብጽ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከኡራጓይ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርግ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት 44 ግቦች ያስቆጠረውን ሞሃመድ ሳላህን በጨዋታው እንደሚያዩት ብዙ ግብጻውያን ተስፋ ያደርጋሉ።