ብሩንዲ በፈረንሳይ ኤምባሲ ለእርዳታ የተበረከቱላትን አህዮች ስድብ ነው በማለት አጣጣለች

አህዮች የብሩንዲ ተወላጆች አይደሉም

የፈረንሳይ ኤምባሲ በብሩንዲ ጊቴጋ መንደር ለሚኖሩ ሰዎች አስር አህዮችን በእርዳታ መለገሱን ተከትሎ፤ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ፒኤሬ ንኩሩንዚዛ አማካሪ ዘለፋ ነው ሲሉ ለ ኤ ኤፍ ፒ ገለፁ።

የግብርና ሚኒስቴር ሴቶችና ህፃናት ላይ የሚሰራ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅትን ወክሎ አህዮቹ ከጎረቤት አገር ታንዛኒያ እንዲገዙ ጠይቋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በሴቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ ሴቶችና ህፃናት የግብርና ውጤቶችን፣ ውሃ ፣ እንጨትና ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዲያመላልሱበት በማድረግ ሸክማቸውን ለማቅለል በማለም ነበር አህዮቹን ለመግዛት እቅድ ውስጥ የገባው።

የግብርና ሚንስትርሩ ዲዮ ጋይድ ሩሬማ ያለ ምንም ሂደት አህዮቹ ከተሰጡበት አካባቢ በአስቸኳይ ተሰብስበው እንዲመጡ የአካባቢው አስተዳዳሪ እንዲያስተባብሩ ጠይቀዋል።

የብሩንዲ ምክርቤቱ ፕሬዚዳንት ቃለ አቀባይ የሆኑት ጋቢይ ቡጋጋ በበኩላቸው "ፈረንሳይ ወደ አህያ ደረጃ አውርዳናለች ፤እውነት ለመናገር አህያ የምን ምልክት ነው?" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።

የፈረንሳይ አምባሳደር ሎረንት ደላሆውሴ በበኩላቸው "እያንዳንዱ ሒደት የታወቀ ነበር ፤ ይህም አዲስ ነገር እንዳልሆነና ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ፕሮጀክት ከቤልጂየም በተገኘም እርዳታ በምስራቅ ሩይሂ ግዛት ተመሳሳይ ድጋፍ ተደርጓል ፤ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጣቸውም" ብለዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአውሮፓ ዲፕሎማት ፈረንሳይ ከወራት በፊት በብሩንዲ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ላይ ትችት በመሰንዘሯ ምክንያት ለእርሱ የተሰጣት አፀፋዊ ምላሽ ነው ሲሉ ለ ኤ ኤፍ ፒ ተናግረዋል።

ፈረንሳይ በህዝበ ውሳኔው ላይ ህገ መንግስቱ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ቆይታን በማራዘም እስከ አውሮፓውያኑ 2034 ድረስ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸው ነው በማለት መተቸቷ የሚታወስ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች