አንድ ሚሊዮን ፈረንሳዊያን ማጨስ አቆሙ

በፈረንጆች 1970ዎቹ ትምባሆ ማጤስ እንደ ዝመና የሚታይበት ዘመን ነበር። የዚያ ዘመን እውቁ ሙዚቀኛ ሰይሽ ገኒሽቡህ (Serge Gainsbourg) ከአፉ ትምባሆ ተለይቶት አያውቅም ነበር። Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በፈረንጆች 1970ዎቹ ትምባሆ ማጤስ እንደ ዝመና የሚታይበት ዘመን ነበር። የዚያ ዘመን እውቁ ሙዚቀኛ ሰይሽ ገኒሽቡህ (Serge Gainsbourg) ከአፉ ትምባሆ ተለይቶት አያውቅም ነበር።

በፈረንሳይ የአጫሾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ባለፉት ዐሥርታት ከሕዝበ ፈረንሳዊያን በእንዲህ ያለ ቁጥር የትምባሆ አጫሾች "በቃን" ሲሉ ታይቶም፣ ተሰምቶም አይታወቅም።

የፈረንሳይ ጤና ቢሮ ባካሄደው በዚህ ጥናት እንዳመለከተው አፍላ ወጣቶች፣ ጎረምሶች፣ እንዲሁም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች በአያሌው ማጤስ ማቆማቸውን ጠቁሟል።

ጥናቱ ይህ ውጤት እንዴት ሊመዘገብ እንደቻለ መላምቱን ጨምሮ ያስቀመጠ ሲሆን ፈረንሳይ ባለፉት ዓመታት በትምባሆ አሉታዊ ውጤቶች ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ዘመቻዎችና እርምጃዎች መውሰዷን ጠቅሷል።

ፈረንሳይ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ትምባሆ ማጤስን የሚያቆሙ ዜጎቿን የሚያበረታቱ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዷን ያስታወሰው ጥናቱ ከነዚህ መሐል የሲጃራ ዋጋን መቆለልና ከሲጃራ ነጻ የሆነ ወር በአገር አቀፍ ደረጃ ማወጅን ይጨምራል።

ይህ የናሙና ጥናት እንዳመላከተው በ2017 ብቻ ዕድሜያቸው ከ18-75 የሆኑ 26.9% በየዕለቱ አጫሽ የነበሩ ሲሆን ከዚያ ቀደም ባለው ዓመት ግን 29.4% አጫሽ ነበሩ።

በዚህም መሠረት 13.2 ሚሊዮን አጫሾች የነበሩባት ፈረንሳይ ቁጥራቸው በአንድ ሚሊዮን ቀንሶ 12.2 ሚሊዮን የትምባሆ ወዳጆች ብቻ ቀርተዋል።

በዓለም ደረጃ ከአስር ሰዎች ሞት የአንዱ ትምባሆን ከመማግ ጋር የተያያዘ ነው። ከነዚህ ሟቾች ግማሾቹ የሚገኙት ደግሞ በቻይና፣ በሕንድ፥ በአሜሪካና በራሺያ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጧል።

ተያያዥ ርዕሶች