"አጭሩ የሥልጣን ቆይታ የእኔ ነው" ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እና የፓርቲያቸው አርማ Image copyright Yilikal Getnet

የኢንጂነሩ የፓርቲ ቅብብሎሽ አስር ዓመትን ይሻገራል። ከነበሩባቸው ሁለት ፓርቲዎች ወጥተው ሌሎች ሁለት ፓርቲዎችን አዋልደዋል።

ከ"አንድነት ለነፃነትና ለዲሞክራሲ" ውስጥ "መርሕ ይከበር" የሚለው ቡድን ሲፀነስ ፊታውራሪ ነበሩ። መርሕ ይከበር ሠማያዊ ፓርቲን ሲፈጥር ሊቀመንበር ሆኑ። የኋላ ኋላ ከሠማያዊ ፓርቲ ማኀጸንም አዲስ ፓርቲ ተጸንሷል። በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ካገኘው ሠማያዊ ፓርቲ ጀርባ የእርሳቸው ጠንካራ አመራር ነበር። ፓርቲው ሲሰነጠቅም እጃቸው አለበት።

ከሰሞኑ አዲስ ፓርቲ ይዘው ብቅ በማለታቸው ብዙዎችን አስገርመዋል።

የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ ወይም በምኅጻረ ቃሉ 'ኢሃን' የሚል ስም የተሰጠው የኢንጂነር ይልቃል አዲሱ ፓርቲ በይፋ መመሥረቱ የተገለጸው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

ቢቢሲ ለምን አዲስ ፓርቲ መመሥረት አስፈለገዎ? ሲል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።

እርሳቸው እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝብ የለውጥ ፍላጎት እየተቀጣጠለ መምጣቱና የሕዝቡን ፍላጎት አደራጅቶ በትግልና በሐሳብ የመምራት ውስንነት በመኖሩ ይህን ኃላፊነት ሊሸከም የሚችል ፓርቲ መመሥረት የግድ ሆኗል።

ጨምረው እንደሚያብራሩትም ''ሥርዓቱ ከሚከተለው የአውዳሚነት ፖለቲካና ተቀናቃኞችን አንደ ጠላት ስለሚመለከት አንድም ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የሚችል የፖለቲካ ማኅበር አንዳይፈጠር አድርጎ ቆይቷል'' ኢሃን ይህን ክፍተት እንደሚሞላ ኢንጂነር ይልቃል ተስፋ ያደርጋሉ።

'በገቢር አናሳ በቁጥር "መቶ አምሳ" የሚሆኑ ፓርቲዎች በአገሪቱ እያሉ የእርስዎ አዲስ ፓርቲ ይዞ መምጣት ምን ይፈይዳል?' በሚል ቢቢሲ ላነሳላቸው ጥያቄ ኢንጂነር ይልቃል ጥያቄውን በመኮነን ምላሻቸውን ይጀምራሉ።

"ጥያቄው መሆን ያለበት ምን ያህል ትሠራላችሁ? ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል? ምን ታሳካላችሁ እንጂ በዚህ አገር የፖለቲካ ማኀበር ምሥረታ አስፈላጊነት ላይ እንዴት ጥያቄ ይነሳል?" ሲሉም ጥያቄ በጥያቄ ይመልሳሉ።

አፍቅሮተ ሥልጣን?

ኢንጂነር ይልቃል ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ ከመሠረቱት አንድነት ለነፃነትና ለፍትሕ ፓርቲ ጀምሮ በገቡበት ፓርቲ ሳይጸኑ ቆይተዋል። እንደ አመራርም እንደ አባልም በቆዩባቸው ፓርቲዎች ውስጥ እንዳለመታደል ሆኖ አምባጓሮ አልተለያቸውም።

ከዓመት ተኩል በፊት ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር የገቡት ቅራኔ ለገላጋይም አስቸጋሪ ነበር።

"በሚመሠርቷቸው ፓርቲዎች ውስጥ ለምን አይረጉም?" ሲል ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ ኢንጂነር ይልቃል ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ይልቃል ፓርቲዎችን ሲቀያይር ምን ነበር ምክንያቱ። በአጠቃላይ የተቃዋሚ ፖለቲካ ውስጥ የይልቃልን ልዩ የሚያደርገው ምንድነው? ብሎ መጠየቅ አይቀድምም?" የሚሉት ኢንጂነር ይልቃል ከጅምሩ ይህን ጥያቄ የሚያነሱት አብረዋቸው የተዋደቁ፣ የታሠሩ፣ የተገረፉ ቢሆኑ ትኩረት ይሰጡት እንደነበር ያወሳሉ።

"እኔን የሚያውቁ ሥልጣን ፈላጊ ብለውኝ አያውቁም" ካሉ በኋላ "ይህ ሩቅ ካሉና ከማላውቃቸው ሰዎች የሚነሳ ነገር ነው" ይላሉ። "ለመሆኑ...ፓርቲ አካባቢስ ምን ጥቅም አለ?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

"በአሁኑ ጊዜ ባለሙያ ሆኖ መሥራት በጣም ብዙ ገንዘብ የሚገኝበት ነው። የፖለቲካችን አለማደግና ፍረጃ ነው እንጂ አውነት ለመናገር አንድ የግል ሕይወቱን ለመምራት የሚፈልግ ሰው [ለጥቅም ሲል] የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ይገባል ብዬ አላስብም።"

"አጭሩ የሥልጣን ቆይታ የኔ ነው"

ኢንጂነር ይልቃልን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሦስት ፓርቲዎችን መቀያየራቸውን ተከትሎ፤ በአመራርነት ካልሆነ ፓርቲ ውስጥ ለመሥራት ፈቃደኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደሆነ ከቢቢሲ ለተነሳላቸው ጥያቄ ከሌሎች የፓርቲ አመራሮች ጋር ራሳቸውን በማነጻጸር ምላሽ ሰጥተዋል።

"ብርሃኑ ነጋ በትወስድ እንደምሳሌ ከኢህአፓ ጀምሮ፣ ከቀስተ ደመና ጀምሮ፣ ከቅንጅት ጀምሮ ስንት ዓመት አለ? የኢዴፓ መሪ ዶ/ር ጫኔ ሁለት "ተርም" ሙሉ አለ። ልደቱ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ዋና ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ አለ። ይልቃል ግን የቆየው ሦስት ዓመት ብቻ ነው። ከዚያም በኋላ ስሙ ጠፍቶና ሌባ ነህ ተብሎ ተባሮ መጥፋት ነበረበት?"

"እንዲያውም በኢትዯጰያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም አጭር ጊዜ በኃላፊነት የቆየው ማን ነው ብለህ ብትጠይቅ ይልቃል ነው።"

ኤርትራን ያካተተው አርማ

በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲተች የነበረው የአዲሱ ፓርቲያቸው መለያ አርማ (ሎጎ) የኢትዮጵያና የኤርትራን ካርታ አጣምሮ የያዘ ነበር።

"አንዲት ሉአላዊት አገርን በካርታ ማካተቱ አግባብ ነው ወይ" ተብለው የተጠየቁት ኢንጂነር ይልቃል፤ አርማው የኤርትራንና የኢትዮጵያን የሕዝቦች ትስስር ለማጉላት ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑና ሆኖም በችኮላ በመሠራቱ በተለይም ሁለቱን አገራት የሚለይ መስመር በጉልህ አለመታየቱ ለትችት እንዳጋለጠው አምነዋል።

"ችቦዎቹ 14 ነበሩ። በኋላ አራት እንዲሆኑ አድርገናል። የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም አቅጣጫ ለነፃነትና ለእኩልነት በአንድነት ሲቆሙ የሚያሳይ ምልክት ነው። ሆኖም አርማው በጉባኤ ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበት እንዲስተካከልና መስመሩ ግልጽ ሆኖ እንዲወጣ ውሳኔ ተሰጥቶበታል" ብለዋል።

ስለ ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ምን ያስባሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየመድረኩ የሚሰጡትን ተስፋ በጥንቃቄ እንደሚመለከቱት የሚናገሩት እንጂነር ይልቃል አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በተለየ ሁኔታ የሚያዩበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል።

"ፓርቲያቸው ነው የሰየማቸው። በሊመንበርነት የመረጧቸው የፓርቲው አራት ግንባሮች ናቸው። የሕዝብ ስሜትን ይይዝልኛል ብለው የሚያስቧቸው ነገሮች ላይ ብቻ አትኩረው እየሄዱ ስለሆነ እኔ እንደውም [የጠ/ሚሩ ንግግሮች] ከማዘናጋት ያለፈና የአገሪቷን ችግር እንዲከማች ከማድረግ ያለፈ ሆኖ አይታየኝም" ይላሉ።

"ፖለቲከኛ በመሆኔ በስሜታዊ ንግግሮች ወይም ደግሞ የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ በሚወሰዱ ትናንሽ እርምጃዎች አላምንም፤ [አንድን መሪ] በመዋቅር በሚሠራው ሥራ ነው የሚለካው" ብለዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ከአቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ጋር ከተደረገ ቃለ ምልልስ ውስጥ የተወሰደ

" 'ኢንጂነር' በሚለው የማዕረግ ስም ለምን ይጠራሉ?"

ከደቡብ ዩኒቨርስቲ በእርሻ ምሕንድስና በመጀመርያ ዲግሪ የተመረቁት ኢንጂነር ይልቃል በመጨረሻ ስለሚጠሩበት ማዕረግ ዙርያ ከቢቢሲ ጋር ቃለምልልስ አድርገው ነበር።

"ቀኛዝማች፣ ግራዝማች ባላንባራስ እየተባለ በኖረ አገር ይህንን ነገር ቁምነገር ያደርጋል ብዬ አላስብም። እኔ በበኩሌ ብዙ አልወደውም። ዞሮ ዞሮ ግን ከውሀ ሀብት ልማት የሞያ ፍቃድ ወስጄ ነው ያለሁት። እኔም ማዕረጉን አልወደውም። ደስተኛም አይደለሁም።

ቢቢሲ፦ ይህንን ቃለመጠይቅ ስናደርግልዎ ኢንጂነር እያልኩ ነው የቆየሁት፤ በዚህ ማዕረግ አትጥሩኝ ብለው ያውቃሉ?

ኢንጂነር ይልቃል፦ እንደነገርኩህ መመጻደቅ እንዳይሆን እንጂ መድረክ ላይ ስብሰባም ስናደርግ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። ለምሳሌ አሜሪካን አገር ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ጋር አንድ መድረክ ላይ ስብሰባ ተቀምጠን እኔ ይሄንን ነገር እንደማልወደው መቅረትም እንዳለበት ተናግሪያለሁ።"

"...ኦባማ በከንስቲትዩሽናል ሎው ፒኤችዲ አላቸው። ነገር ግን "ዶ/ር ኦባማ" ብለናቸው አናውቅም። ሰው ታይትል ኦሪየንትድ ነው። እኔም አልፈልገውም። እንዲሁ መመጻደቅ እንዳይሆና ከሌሎች ሰዎች ላለመለየት ነው ዝም የምለው።"

ቢቢሲ፦ ግን እኮ ኢንጂነር ይልቃል! የሚጠራው ሰው ዝም ካለ ወይም በዚህ ማዕረግ አትጥሩኝ ካላለ ፈቅዶታል አያስብልም?

ኢንጂነር ይልቃል፦ በቃ ከዛሬ ጀምሮ ይልቃል ብለህ ጥራኝ።

ተያያዥ ርዕሶች