ቀዶ ህክምና በአፍሪካ ስጋት መሆኑ ከፍ ብሏል

ባለሙያዎች በቀዶ ህክምና ላይ Image copyright AFP

በአፍሪካ ቀዶ ህክምና የሚያካሂዱ ህሙማን ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር የመሞት ዕድላቸው በሁለት እጥፍ የጨመረ እንደሆነ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ነገሮችን ይበልጥ አስከፊ የሚያደረገው ደግሞ ይላሉ ተመራማሪዎቹ፤ ቀድመው ቀጠሮ ተይዞላቸው የሚደረጉ ቀዶ ህክናዎች ቁጥር ትንሽ መሆኑ ነው።

የሚካሄዱ ቀዶ ህክምናዎች ቁጥር ካለው የህክምና ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር በሃያ እጅ ያነሰ ነው። ለዚህም ነው ድምጽ አልባው ገዳይ የሚሉት።

ከኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የመጡት እና የጥናቱ ተባባሪ ፕሮፌሰር ብሩስ ቢካርድ እንደሚሉት የችግሩ ዋና መንስኤ የጤና ባለሙያ እጥረት እና ችግሩን ቀድሞ ያለመለየት እንደሆነ ይናገራሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዶ ህክምና ከሚያካሂዱ ህሙማን 1በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱ ሲሆን፤ በአፍሪካ ግን ቁጥሩ ወደ 2.1 በመቶ ከፍ ይላል።

ምንም እንኳን ህመምተኞቹ በእድሜ ወጣት እና ከባድ የሚባል የጤና ችግር ያለባቸው ባይሆኑም፤ ከቀዶ ህክምና በኋላ የመሞታቸው እድል ከፍ ያለ ነው።

በአፍሪካ በብዛት የተለመደውና 33 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው 'ሲ ሴክሽን' የሚባለው ልጅን በቀዶ ህክምና መውለድ ነው። ይህ ቀዶ ጥገና ብዙ ጊዜ ለኢንፌክሽን የተጋለጠና እናቶቹን ለሞት የሚዳርግ ነው።

በአይነቱ ትልቅ የተባለው ጥናት ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ግብፅን ጨምሮ ሃያ አምስት የአፍሪካ ሃገራትን የሸፈነ ሲሆን ከ11 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ነበሩት።

ቀላል የሚባል ቀዶ ህክምና እንኳን ያካሄዱ አፍሪካውያን ከላይ በተጠቀሱት ምክነያቶች ብቻ ይሞታሉ።

ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ከ10 ሰዎች አንዱ ብቻ የቀዶ ህክምና ህክምና ያገኛል። አገልግሎቱን ማግኘት ከባድ ቢሆንም፤ ከቀዶ ህክምናው ጋር የተያያዙ ችግሮች ግን ብዙ ናቸው።

ይሄ ሁሉ ታዲያ የሚያያዘው ከደካማ የጤና ሥርዓት፣ የባለሙያዎች ቁጥር ማነስ እና ታካሚዎቹ በጊዜ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት አለማግኘታቸው ነው ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

የቀዶ ህክምና ደግሞ ሁሌም ቢሆን ከህክምናው በኋላ ያለው እንክብካቤ ወሳኝነት አለው፤ ምክነያቱም በቀላሉ ወደ ሌላ ህመም ሊቀየር ስለሚችል።

ታካሚዎቹ ከህክምናው በኋላ ጥብቅ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ አገልግሎቱ ከሚሰጥበት የጤና ማዕከል በብዙ ርቀት ላይ ስለሚኖሩ ቀጠሯቸውን አክብሮ ባለሙያ ጋር መምጣት ከባድ ነው።

ይህ እና ሌሎች ምክነያቶች ተደማምረው የታካሚዎቹን ከቀዶ ህክምና በኋላ የመሞት ዕድልን ይጨምረዋል እላል የአጥኚዎቹ ድምዳሜ።

ተያያዥ ርዕሶች