በተዓምር የተረፈው ሕጻን ወላጆች የት ነበሩ?

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ማላዊው ስደተኛ ጋሳማ ማማዱ ከፈረንሳይ ፖሊስ የክብርና የጀግንነት የምሥክር ወረቀት ተበርክቶለታል።

በፓሪስ ከሰሞኑ ከ4ኛ ፎቅ ከመፈጥፈጥ የተረፈው ሕጻን ወላጆች ማላዊውን ስደተኛ "እግዜር ይስጥልን" ብለውታል።

"ከልቡ ጀግና ነው።" ብለዋል የሕጻኑ ሴት አያት።

የማላዊው ስደተኛ ጀብድ ዓለምን ካስደመመ በኋላ አዳዲስ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል።

የብዙዎች ጥያቄ እንዴት የ4 ዓመት ብላቴና በረንዳ ላይ በዚያ ሁኔታ ተንጠላጥሎ ሊገኝ ቻለ"? "ወላጆቹስ ይህ ሁሉ ሲሆን የት ነበሩ?" የሚለው ነው።

Image copyright AFP/Getty

የልጁ አባት ጌም እየተጫወተ ነበር

የብላቴናው አባት በወቅቱ አንዳንድ ዕቃ ሊገዛዛ ወደ ገበያ መውጣቱ የተነገረ ሲሆን ሕጻኑን በዚያ ቸልተኝነት ጥሎ በመውጣቱ ውግዘት እየደረሰበት ነው።

ብላቴናው ሪዩኒየን ከሚባለውና አያቱና እናቱ ይኖርበት ከነበረው አካባቢ ወደ ፓሪስ የመጣው ከሦስት ሳምንት በፊት አባቱን ለማግኘት ነበር ተብሏል፤ አባቱ የሥራ ቦታው ፓሪስ በመሆኑ።

የልጁ እናትና ሌላኛው ልጃቸው በመጪው ሰኔ ወደ ፓሪስ ሊመጡ ቀጠሮ ነበራቸው።

የልጁ አባት የሚኖረው 6ኛ ፎቅ ነበር። ሕጻኑ ግን በረንዳ ላይ ተንጠላጥሎ የተገኘው 4ኛ ፎቅ ላይ ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለው ጉዳይ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃንን አሁንም እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

ብላቴናው ከ6ኛ ፎቅ 4ኛ ፎቅ ላይ በዚያ ሁኔታ መገኘቱ ከ6ኛ ፎቅ በመውደቅ ላይ ሳለ 4ኛ ፎቅ ላይ ሲደርስ በአንዳች ተአምር ሽቦ አንጠልጥሎ አስቀርቶት ይሆናል የሚል መላምት እየተነገረ ነው።

እናትየው እንደምትለው ደግሞ የልጁ አባት ሕጻኑን ይጠብቀው የነበረው ብቻውን አልነበረም፤ ጥሎት የሄደውም ለዚሁ ነው።

"ባለቤቴ የፈጸመውን ነገር ማስተባበል አልችልም። ሰዎች ማንም ላይ የሚደርስ ነገር ነው አንቺ ላይ የደረሰው ይሉኛል። ለማንኛውም አሁን ማለት የምችለው ልጄ እድለኛ መሆኑን ነው።"

አባት ልጁን ጥሎ ገበያ ከሄደ በኋላ ወዲያውኑ ወደቤት ከመመለስ ይልቅ ጌም ለመጫወት መቆመርያ ቤት ጎራ ሳይል አልቀረም።

ጎረቤቶቹ የት ነበሩ?

4ኛ ፎቅ የነበሩ ጎረቤቶቹ ሕጻኑን ለማዳን ለምን ዘገዩ? ደግሞስ ማሊያዊው ስደተኛ ማማዱ ከምድር ተነስቶ እንደ ፌንጣ እየዘለለ 4ኛ ፎቅ እስኪመጣ ድረስ እንዴት እርዳታ ማድረግ ተሳናቸው የሚለው ሌላው መነጋገሪያ ሆኗል።

የ4ኛ ፎቅ ነዋሪዎች ለፓሪሲያን ለተሰኘ ጋዜጣ እንደተናገሩት አንደኛው ጎረቤታቸው የልጁን አንድ ክንድ ይዞ እንዳይወድቅ ለማድረግ የቻለ ቢሆንም ሳብ አድርጎ ወደ በረንዳው ለማምጣት በበረንዳዎቹ መካከል ያለው ክፍት ቦታ እንዳስቸገረው ተናግሯል።

"ነገሮችን ቀስ በቀስ ማድረጉ ይሻላል ብዬ ነው። አንጠልጥዬ ወደ በረንዳው ለማስገባት ብሞክር ልጁ ይወድቅብኛል የሚለው ፍርሃት አደረብኝ" ይላል ጎረቤቱ።

ብላቴናው በወቅቱ የስፖይደርማን ልብስ ለብሶ መታየቱ አግራሞትን ፈጥሯል። በወቅቱ አውራ ጣቱ ላይ እየደማ እንደበረና ሚስማር ክፉኛ እንደቧጨረውም ተነግሯል።

ብላቴናው አሁን የት ነው ያለው?

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሕጻኑን ማገገሚያ አስቀምጠው ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኝ እያደረጉት ነው ተብሏል። አባትየው በሆነው ነገር እጅግ ሐዘን ገብቶታል፤ ለጊዜውም ከዕይታ ተሰውሯል ተብሏል።

ወላጆቹ በቸልተኝነት ላደረሱት ጉዳት የ2 ዓመት እስርና 30 ሺ ዩሮ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችልም ተነግሯል።

የአዳጊው ሴት አያት በበኩላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሉን ሲመለከቱ እጅግ መደንገጣቸውን ለፈረንሳይ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

"የፈጣሪ ያለህ! እንዲህ ደንግጬ አላውቅም! ደግነቱ ነፍስ አዳኙ እንዴት መንጠላጠል እንዳለበት አሳምሮ ያውቃል። ብዙ ሰዎች ምድር ላይ እጃቸውን አጣምረው ቆመው ነበር። የማይታመን ጀብድ ነው የፈጸመው፤ ከልቡ ጀግና ነው!" ሲሉ አሞካሽተውታል።

ጋሳማ ማማዱ ማን ነው?

የ22 ዓመቱ ማማዱ ማላዊ ዜግነት ያለው ሲሆን አገሩን ለቅቆ ወደ ምዕራብ አፍሪካ የሄደው ግን በልጅነቱ ነው።

በኋላም የሰሀረ በረሃን፣ ቡርኪናፋሶን ኒጀርን እና ሊቢያን አቋርጦ በሜዲትራኒያን ሰንጥቆ ጣሊያን የገባው በ2014 ነው። የተሳካ ስደት ከማድረጉ በፊት በፖሊስ ተይዞም ያውቃል።

ማማዱ ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማርኮን እንደተናገረው ፈረንሳይ የመጣው ጣሊያን ውስጥ ማንንም ሰው ስለማያውቅና ወንድሙ ግን ፈረንሳይ ይኖር እንደነበር አብራርቷል።

አዳዲስ በሚገነቡ ሕንጻዎች አካባቢ ግብርን በመሸሽ ዝቅተኛ ሥራ በመሥራት ይተዳደር እንደነበረና ማታ ማታም አልቤርጎ እያደረ ሲኖር መቆየቱንም ለፈረንሳይ ፕሬዝዳንት አብራርቶላቸዋል።

ማማዱ እንደሚለው ጥገኝነት ለማግኘት ማመልከቻ አስገብቶ አያውቅም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ