አልሲሲ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ

አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሰሞኑ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሰሞኑ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለሁለተኛ ጊዜ በሥልጣን ለመቆየት ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። አልአህራም ጋዜጣ እንደዘገበው የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓቱ በፈረንጆቹ ሰኔ 2 ይፈጸማል።

ባለፈው ኅዳር በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አልሲሲ 97 ከመቶ ድምጽ በማግኘት ነበር ያሸነፉት።

የአልሲሲ ቃለ መሐላ በአገሪቱ ምክር ቤት እንደሚፈጸምና ይህም ሆስኒ ሙባረክ በፈረንጆቹ 2005 ዓ.ም ለ5ኛ ጊዜ ቃለ መሐላ ከፈጸሙ ወዲህ በአገሪቱ ሸንጎ የሚካሄድ የመጀመርያው የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ይሆናል ብሏል፣ አልአህራም።

በዚህ በዓለ ሲመት የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ እና ዓለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት ይታደሙታል ተብሎ ይጠበቃል።

በኅዳሩ ምርጫ አልሲሲ ማሸነፋቸው ከውድድር በፊትም ቢሆን እንዲጠበቅ ያደረገው ተፎካካሪያቸው እምብዛምም በሕዝብ ዘንድ የማይታወቁ የነበሩና ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊትም የአልሲሲን ዳግም መመረጥ በይፋ ይደግፉ የነበሩ ሰው መሆናቸው ነው።

የአልሲሲ ተቀናቃኞች ሰውየው አፋኝና አምባገነን ናቸው ሲሏቸው ደጋፊዎቻቸው በአንጻሩ ለአገሪቱ መረጋጋትን አምጥተዋል ብለው ያሞካሿቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች