ልጅነቴን ያያችሁ? በተለያዩ የኢትዮጵያ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሕፃናት ሁኔታ

ህፃናት በሰሜን ሶማሊያ የሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ (2012)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ህፃናት በሰሜን ሶማሊያ የሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ (2012)

በኢትዮጵያ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች በሚዋሰኑ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች መካከል ያጋጠሙ ግጭቶችና በጸጥታ ኃይሎች ሳቢያ ሲደርስ በነበረዉ ጥቃት በርካቶች ከቀዬቸዉ በመፈናቀል እስከ ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ ድረስ ተሰድደዋል።

በሁለቱም ክልሎች የነበረዉ ግጭት 93ሺ የሚጠጉ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸዉ ሲያፈናቅል እድሜያቸዉ ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ደግሞ ትምህርታቸዉ እንዲያቋርጡ ተገደዋል ይላል ጥር ወር 2018 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣዉ ሪፖርት።

ሌሎች ከ1ሺ 500 በላይ ህጻናት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸዉ ተለያይተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች እንዲሰፍሩ ሆኗል።

ልጅነትና መፈናቀል

ግጭቶች ሕጻናቱን ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ፣ በወላጆቻችው የቅርብ ክትትልና ክብካቤ እንዳያገኙ እንዲሁም እንደልጅ ቦርቀው እንዳያድጉ እያደረገ ነው።

ወይዘሮ ፈቲሃ አደም ተወልደዉ ከአደጉባት ከተማ ጅግጅጋ የስምንት ወር ሕጻን ይዘው ነው መስከረም ሁለት ግጭቱን ሸሽተው ወደ ሐመሬሳ መጠለያ የመጡት። እኚህ ወይዘሮ ከኑሯቸው መፍረስ ከገቡበት ጉስቁልና ይበልጥ የልጃቸው ጤንነት ያሳስባቸዋል።

"ይህ ነዉ ብዬ ለመግለጽ በሚያስቸግረኝ ሁኔታ ነው ከቤት ንብረቴ ሕጻን ልጄን ይዤ የተፈናቀልኩት፤ ያለ ምግብ ያለ ውሃ ጅግጅጋ ካምፕ ለሁለት ቀናት ካሳለፍን በኋላ ሕጻናት እየተቸገሩ እላያችን ላይ እየታመሙ ወደ ሐማሬሳ መጣን፤ ቆይቶ ደግሞ በየወረዳችሁ ግቡ ተብለን በድሬ-ጥያራ ገባን" ይላሉ።

እኚህ እናትን ጨምሮ ከ8 እስከ 10 ቤተሰብ የያዙ በርካቶች ለጤንነታቸዉ አስጊ በሆነ ቦታ ሕጻናት ልጆችን ይዘው እየኖሩ ነው።

"ምንም የጤና አገልግሎት ስለሌለ ልጆቻችን በጣም ችግር ላይ ናቸው" የሚሉት ወይዘሮ ፈቲሃ "ያለንበት ቦታ በደን የተሸፈነና ከሸክላ የተሰራ በመሆኑ ልጄ እስካሁን ድረስ እየታመመ ነው፤ እዚህ ብዙ ህጻናት አሉ፤ መጥቶ የሚያየን ሰው ግን የለም" ሲሉ ያማርራሉ።

በግጭቶቹ ምክንያት ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ የነበሩ አብዛኛዎቹ እንደወጡ የሚናገሩት የአደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ለቀሩት ምላሽ የመስጠት ሥራው እየተሰራ እንደሆነ ነው የሚገልጹት።

"እስከ አሁን መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ እናቶችና ሕጻናት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ታች ካሉ የጤና ሴክተሮች በመተባበር የጤና እንክብካቤ እያደረገ ነው የሚገኘው። ከዚህ ባለፈ ኮሚሽኑ ሕጻናት እንዳይጎዱ አልሚ ምግብን ያቀርባል" ይላሉ።

መጠለያ ሰርተን እናስገባችኋለን ተብሎ እስከ አሁን ተስፋ ያለዉ ነገር ለማየት አልታደልንም የሚሉት ወይዘሮ ፈቲሃ ግን የተሻለ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻልንም ሲሉ የኮሚሽነሩን ኃሳብ ይሞግታሉ።

አያይዘውም "ልጆቻችን የሚበሉት ነጭ ሩዝ ብቻ ነው፤ የተሻለ የጤና አገልግሎት እዚህ መጠለያ ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ መፍትሄ እንፈልጋለን" ይላሉ።

በኢትዮጵያ ሴቭ ዘ-ችልድረን የሰብዓዊ ምላሽ ኃላፊ የሆኑት ሀሰን አብዱላሂ እነዚህ ተፈናቃዮች ያላቸውን ነገር ስላጡ ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ሥራዎች ላይ ለመሰማራት የተገደዱበት አጋጣሚ አለ ይላሉ።

አክለውም "ግጭት በተነሳባቸዉ አካባቢዎች መጀመርያውንም ድርቅ ስለነበረ የአመጋገብ ሁኔታቸው ወርዶ የታየበት፣ ለአካልና ጾታዊ ጥቃት የተዳረጉበትና ቤተሰባቸውን ለመርዳት ያለ እድሜያቸው እንዲያገቡ የተገደዱበት ሁኔታም እንዳለ ያካሄድነው ጥናት ያሳያል" ሲሉ ገልጸዋል።

መልሶ የማቋቋም

እስካሁን ድረስ 300 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ ተመልሰዋል የሚለት የአደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽነር መመለስ ያልፈለጉትን በኦሮሚያ ክልል 11 አካባቢዎችን በመምረጥ መልሶ ለማቋቋም እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። ባቀዱት መሰረት እስከ አሁን ድረስ ከ30 ሺ በላይ መጠለያ ጣብያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ወደተሰራላቸው መጠለያ እንዲገቡ ተደርጓል ሲል ይገልጻሉ።

ሶማሌ ክልል ውስጥ ደግሞ 8 አካባቢዎች ተመርጠዉ በአራቱ መጠለያው ተገንብቶ የተፈናቀሉትን የማስገባት ሥራ ብቻ እንደሚቀርም ገልፀዋል።

መጠለያ ውስጥ ለተቀሩት ሰዎች አገልግሎት በመስጠት ረገድ ግን ክፍተቶች እንዳሉ ኮሚሽነሩ ይቀበላሉ።

"ሰዎች ከመጠለያ ጣቢያ አውጥቶ በዘላቂነት በማቋቋም ክፍተቶች አሉ።"

በኢትዮጵያ ሴቭ ዘ-ችልድረን የሰብዓዊ ምላሽ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሀሰን በበኩላቸው በቀጣይነት የሕጻናትን ሁኔታ ለመጠበቅ፣ ግጭትን ለመከላከልና ለግጭት ተጋላጭ የሆኑትን ቦታዎች ላይ ግጭት የመከላከል ስራዎች መሰራት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።