ዴንማርክ ሙሉ የፊት ገጽታን የሚሸፍን 'ሂጃብ' አገደች

ከዐይን በስተቀር ሙሉ ፊትን የሚሸፈነውን ኒቃብ ለብሰው የሚታዩ ሴቶች በአውሮፓ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ኒቃብ የለበሱ ሴቶች በአውሮፓ

ዴንማርክ ሙስሊም ሴቶች ሙሉ ፊታቸውን የሚሸፍነውን ኒቃብ ወይም ቡርቃ በመባል የሚታወቀውን የሂጃብ አለባበስ በሕግ ከልክላለች። ሕጉ በ73 ድጋፍና በ30 ተቃውሞ ነው የጸደቀው።

ከነሐሴ 1 ጀምሮ ሕጉ ተግባራዊ ይሆናል።

ኒቃብ ወይም ቡርቃ የሚለብሱ ዴንማርካዊያን ወይም የአገሬው ነዋሪዎች አንድ ሺህ ክሮነር ወይም 157 ዶላር ቅጣት ይጣልባቸዋል። ሆኖም በተደጋጋሚ ለቅጣት የሚዳረጉ ዜጎች የቅጣቱን 10 እጥፍ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።

የሕጉ አንቀጽ በግልጽ 'ሙስሊም ሴቶች' የሚል አንቀጽን ባያካትትም የኒቃብና የቡርቃ ሂጃብ ኢስላማዊ አለባበስ በመሆኑ ይህንኑ ለማስቆም የሚሞክር ሕግ እንደሆነ ይታመናል። 'ማንም ሰው ሙሉ ፊቱን የሚሸፍን ልብስ በአደባባይ ለብሶ ከተገኘ ይቀጣል' የሚል ሐሳብን የያዘ አንቀጽ በሕጉ ተካቷል።

የሕጉን መጽደቅ ተከትሎ የዴንማርክ ፍትሕ ሚኒስትር ሶረን ፔፕ እንዳሉት 'በኛ ዴንማርካዊያን ባሕል ሰዎች የፊት ገጽታን እየተያዩ ነው የሚያወጉት። ዐይንና ፊትን ሸፍኖ ማውጋት የእኛ እሴት አይደለም' ብለዋል።

የመብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ሕጉ የሴቶችን መብት የሚጻረር ብሎታል።

የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ቤልጂየም ተመሳሳይ ሕግ ለማጽደቅ በምትሞክርበት ወቅት ይህ ዓይነቱ ሕግ 'የዜጎችን የእምነት ነጻነትና አብሮ የመኖርን እሴት የሚንድ' በሚል አግዶት ቆይቶ ነበር።

ቡርቃ-ኒቃብ የከለከሉ አገራት

ኒቃብና ቡርቃን በሕግ በመከልከል ፈረንሳይን የቀደማት የለም። በሚያዚያ 2011 በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሃይማኖታዊ መገለጫ የሆኑ አልባሳት በሙሉ አግዳለች።

ከፈረንሳይ ቀጥሎ ቤልጂየም ማንኛውም ማንነትን ለመለየት አዳጋች የሚያደርግ የፊት ገጽታን የሚሸፍን አለባበስን አግዳለች።

ኦስትሪያ፣ ቡልጋሪያ እንዲሁም የደቡባዊ ጀርመኗ ቤቬሪያ ክፍለ አገር በይዘታቸው ተመሳሳይ የሆኑ ከፊልና ሙሉ ክልከላዎችን በዜጎችና ነዋሪዎች ላይ ጥለዋል።

የኔዘርላንድስ ምክር ቤት በ2016 ተመሳሳይ እግድ ያስተላለፈ ቢሆነም በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይሁንታን እስኪያገኝ እየተጠበቀ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች