የወር አበባ ለምን በአንዳንድ ሴቶች ላይ ህመም ያስከትላል?

የወር አበባ ዑደት

የወር አበባ ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው።

የመተንፈስ ወይም የመመገብ ያህል ከተፈጥሮ ሂደቶች አንዱ ነው። የምድርን እኩሌታ የያዙት ሴቶች ወርሀዊ ዑደትም ነው። ሆኖም ስለ ወር አበባ ማውራት እንደ ሀጢያት ይቆጠራል። ከወር አበባ ጋር የተያያዙ የተዛቡ አመለካከቶችም የትለሌ ናቸው።

ከደቡብ እስያ ሴቶች አንድ ሦስተኛው የወር አበባ ከማየታቸው በፊት ስለ ወር አበባ ምንነት እንደማያውቁ ዩኒሴፍ እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 የሰራው ጥናት ያመለክታል። ከኢራናውያን ሴቶች 48 በመቶዎቹ እንዲሁም ከህንዳውያን ሴቶች አስር በመቶ የሚሆኑት የወር አበባ በሽታ እንደሆነ ያስባሉ።

በዓለም ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ እንስቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ይገለላሉ። ሀፍርትም ይሰማቸዋል።

የግንዛቤ ክፍተቱን ከግምት በማስገባት ዋሽ ዩናይትድ የተባለ የተራድኦ ድርጅት በየአመቱ ግንቦት 28 ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንጽህና ቀን እንዲከበር አድርጓል። ስለ ወር አበባ ርዕሰ ጉዳይ ማውራትን ለማስለመድ ስለ ሂደቱ ማወቅ የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

የወር አበባ ዑደት እንዴት ይፈጠራል?

ስለ ወር አበባ ምንነት ማስገንዘብ ስለ ዑደቱ ያለው አመለካከት እንዲቃና መንገድ ይከፍታል። የወር አበባ ከአስር እስከ 14 ዓመት አንስቶ ከ45 እስከ 50 ዓመት የሚዘልቅ ዑደት ነው።

የወር አበባ ወርሀዊ ዑደት የሚፈጠረው በየ28 ቀን ልዩነት ሲሆን፣ ወደ ጽንስነት ያልተለወጠ እንቁላል ፈርሶ በደም መልክ የሚወጣበት ሂደት ነው። የ28 ቀን ዑደቱ ሁለት ደረጃዎች አሉት።

የመጀመሪያው የወር አበባ ከጀመረበት ቀን አንስቶ ያሉትን ሁለት ሳምንታት ያካትታል። በዚህ ወቅት ከሴቶች መራቢያ ህዋስ በአንዱ እንቁላል ማደግ ይጀምራል። የእንቁላሉን እድገት የሚያፋጥን ሆርሞንም ይመረታል።

ወደ አስራ አራተኛው ቀን አካባቢ እንቁላሉ ሲያድግ በማህጸን ቧምቧ አድርጎ ወደ ማህጸን ይወርዳል። እንቁላሉ ከወንድ ዘር ጋር ከተዋሃደ የእርግዝና ሂደት ይጀመራል። ውህደቱ ካልተፈጠረ እንቁላሉ ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ ሞቶ ይወገዳል።

የዑደቱ ሁለተኛ ደረጃ በአስራ አራተኛው ቀን ጀምሮ በሀያ ስምንኛው ቀን ይጠናቀቃል። በሀያ አምስተኛው ቀን በማህጸን ውስጥ የሚመረተው የሆርሞን መጠን ቀንሶ ከሦስት እስከ ሰባት ቀን ደም ይፈሳል።

በዚህ መንገድ የሚፈጠረው የወር አበባ ወርሀዊ ሂደትን ይከተላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለምን በወር አበባ ወቅት ህመም ይከሰታል?

በወር አበባ ወቅት ምቾት የማይሰማቸው ሴቶች አሉ። አንድ ሦስተኛ ያህሉ ሴቶች ደግሞ ያማቸዋል። ከህመሞቹ ራስ ምታት፣ የጀርባ ህመም፣ ሆድ ቁርጠትና ማቅለሽ ይጠቀሳሉ። ለ24 ሰዓት ሊቆዩም ይችላሉ።

ምክንያቱን ለማብራራት ቢያስቸግርም አቅም ማነስ የሚከሰትበትም ጊዜ አለ።

የወር አበባ ህመም መጠን ያለፈ የማህጸን ውስጥ የደም እጢ ውጤት ነው። ይህም የማህጸን ጡንቻ መወጠርና መላላት የሆድ ቁርጠት ያስከትላል። ህመሙ ከወር አበባ አንድ ወይም ሁለት ቀናት በፊት ጀምሮ ለቀናት ይዘልቃል። አንዳንድ ሴቶች ላይ ከቀናት ሊያልፍም ይችላል።

ዲስሜኖሪያ የተሰኘው ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ፍተኛ የሆድ ቁርጠት እድሜ ሲጨምር ሊከሰት ይችላል። በዘር የመተላለፍ ባህሪም አለው። በማህጸን ውስጥ መሆን ያለባቸው ህዋሶች ከማህጸን ውጪ ሲሆኑ ኢንዶሜትርዮሲስ ይባላል። ከአስር ሴቶች በአንዷ ሊከሰትም ይችላል።