“መሸ መከራዬ”፡ የታዳጊዎች ስቃይ

መድሃኒት ለእከክ በሽታ Image copyright WHO

በኢትዮጵያ በሦስት ክልሎች የተከሰተው የእከክ በሽታ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች ማገርሸቱ ተሰምቷል።

የጥቂቶች ጉዳይ አይደለም። በዓለም 130 ሚሊዮን ሰዎች ቆዳቸውን ያካሉ። እከክ ቀላል የሚመስል ግን ደግሞ ምቾት የሚነሳ የቆዳ ችግር ነው። በዚያ ላይ እረፍት ይነሳል።

ብዙውን ጊዜ የሚኾነው ታዲያ እንዲህ ነው፤ ድርቅን ተከትሎ የውሃ እጥረት ይከሰታል። የውሃ እጥረት ደግሞ ለእከክ መዛመት በር ይከፍታል። በኢትዮጵያም የሆነው ይኸው ነው።

በቅርብ ዓመታት የተከሰተ ድርቅን ተከትሎ በትግራይ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች እከክ በተለይም ብላቴናዎችን እያሰቃየ ነው።

ባለፈዉ ዓመት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የዚህ በሽታ ስርጭት 5.5 በመቶ ነበር። ትግራይ ክልል በበኩሉ ከጥቅምት 2015 እስከ መጋቢት 2016 ባሉት ወራት ብቻ 27ሺህ ነዋሪዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተዋል። በተመሳሳይ ዓመት በአማራ ክልል 373 ሺህ ሰዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተው እንደነበር የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ዓመትም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዳባት ወረዳ ባካሄደዉ አንድ ጥናት በወረዳዉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ 10 በመቶ ሕጻናት የበሽታዉ ተጎጂ እንደሆኑ ያሳያል።

ቦርቀዉ ያልጠገቡ ሕጻናት ሲያኩ ማየት በራሱ ያማል። የነገ ተስፋቸዉ እዉን ለማድረግ ረጅም ርቀት እየተጓዙ የሚማሩ ሕጻናት ቀላል የሚመስለዉ፤ ግን ደግሞ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳቱ የጎላው የእከክ በሽታ ጠምዶ ይዟቸዋል።

ስሙን የማንጠቅሰው የዳባት 03 ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ታዳጊ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጁ ላይ የታየዉ የእከክ በሽታ እንቅልፍ እየነሳው ነው። ቀን ላይም ቢኾን መማር እንደተቸገረ ይናገራል።

"ቆሻሻ ዉሃ ስነካ እጄን ማሳከክ ጀመረኝ። እናቴ ለሕክምና የሚሆን ገንዘብ ስለሌላት ሐኪም ቤት አልወሰደችኝም" ይላል በሚያባባ የልጅ አንደበቱ።

"አስተማሪዋ ደግሞ በሌሎች ተማሪዎች እንዳላስተላልፍባቸው ለብቻዬ አስቀመጠችኝ። ተማሪዎችም ሰላም አይሉኝም፣ አብሬያቸዉ መጫወት አልቻልኩም። ታጋባብናለህ ይሉኛል" ሲል ይህ በሽታ ያሳደረበትን መገለል ይናገራል።

Image copyright WHO

"መሸ መከራዬ!"

የእከክ በሽታ ከ15 ዓመት በታች የሚገኙ ሕጻናትን በብዛት የሚያጠቃ ሲሆን በንጽህና ጉድለት እንደሚመጣ የሕክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ።

ዳባት ወረዳ ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች 50 በመቶ ተማሪዎቹ ከገጠር አካባቢ ነው የሚመጡት። ገጠር ደግሞ በቂ ውሃ የለም። በሽታው በባህሪው ከፍተኛ የሆነ ንክኪ በሚኖርበት አካባቢ ቶሎ ይሰራጫል።

ማታ ላይ የማሳከኩ ሁኔታ ስለሚጨምር ነው የአካባቢዉ ማኅበረሰብ በሽታውን "መሸ መከራዬ" እያለ የሚጠራው።

እከክን ከማከክ ሌላ...?

ይሄንን ችግር ለማጥናት ባለሞያዎቹን ወደ ወረዳዉ የላከ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባደረገዉ የጤና እርዳታ የተወሰኑ ተማሪዎች መድኃኒት ማግኘት እንደጀመሩ የዳባት 03 ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ርስቄ ረታ ወርቁ ይገልጻሉ።

"አብዛኛዎቹ ልጆት እጃቸዉ ላይ ነዉ እየታየ ያለዉ። የተወሰነ ተማሪዎች መድኃኒት አግኝተዋል" ብለዋል። ሆኖም ግን ተማሪዎች ላይ የሚያደርሰውን መሸማቀቅ ሳይጠቅሱ አያልፉም።

ሰላምታ መለዋወጥ እና መተቃቀፍ በደቂቃዎች ውስጥ በሽታው ለመተላለፍ እድል የሚሰጡ በቂ ምክንያቶች ናቸው። ልብስ መዋዋስና የንጹህ ዉሃ አቅርቦት ችግር የመተላለፍ ዕድሉን በእጥፍ ይጨምሩታል።

አብዛኛዎቹ የገጠር ትምህርት ቤቶች በቂ የዉሃ አቅርቦት እንደሌላቸዉ የሚናገረው በጎንደር ዩኒቨርሲ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ መምህር ዶክተር ሄኖክ ዳኜ፤ ኅብረተሰቡ ዘንድ ያለዉ የዚህን በሽታ የተሳሳተ ግንዛቤ በመቀየር ረገድ ብዙ መሠራት እንዳለበት ይገልጻል።

"የቆየ ምግብ በመብላት የሚመጣ ነው፤ እርግማን ነው እያሉ ሰዎች ሕክምና አይሄዱም። ከዚህ አልፎም በዚህ በሽታ የተጠቁት ሕጻናት ተማሪዎች ሌሊት ስለሚያሳክካቸው በቂ እንቅልፍ ስለማያገኙ ቀን እንቅልፍ ስለሚጥላቸው በአግባቡ ለመማር እየተቸገሩ ነው" ይላል ዶክተር ሄኖክ።

ተያያዥ ርዕሶች