ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ያሳፈረችው ጀልባ ሰጠመች

የመን ለአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች ተመራጭ የሆነች ይመስላል

የፎቶው ባለመብት, IOM

ከሶማሊያ ወደ የመን አገር እያቋረጡ የነበሩ 46 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መሞታቸው ተሰምቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎች እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊያኑ ብቻ የተሳፈሩባት ጀልባ በመገልበጧ ነው አደጋው የደረሰው።

ሌሎች 16 ኢትዯጵያዊያን ደግሞ የገቡበት አለመታወቁን የዓለማቀፉ የስደተኛ ጉዳዮች ማኅበር አይኦኤም አስታውቋል።

ከሞት የተረፉ ዜጎች እንዳሉት ከሆነ ድንበር አሻጋሪዎቹ የሚሾፍሯት ጀልባ ቢያንስ አንድ መቶ ኢትዮጵያዊያንን አሳፍራ ነበር።

ጀልባዋ መነሻዋን አድርጋ የነበረው ቦሳሶ ወደብን ነበር።

ስደተኞቹ ኢትዮጵያዊያን በጦርነት በምትታመሰው የመንና በሌሎች የገልፍ አገሮች ሥራ ለማግኘት ያለሙ ነበሩ ተብሏል።

ሁሉም ሰደተኞች ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ይህን አደጋ ልዩ አድርጎታል።

ጀልባዋ የተገለበጠቸው ረቡዕ ማለዳ በገልፍ ኤደን ሲሆን ከሞቿቹ ውስጥ ዘጠኙ ሴቶች ናቸው።

በዚህ የሶማሊያ-የመን መንገድ ቢያንስ 7 ሺህ ስደተኞች በየወሩ ለማቋረጥ እንደሚሞክሩ ጥናቶች ያሳያሉ። ባለፈው ዓመት ብቻ 100 ሺህ ስደተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ ባሕር ለማቋረጥ ሞክረዋል።

የዓለማቀፉ የስደተኛ ጉዳዮች ማኅበር ኃላፊ ሞሐመድ አብዲከር እንደሚሉት ከሆነ ጉዞው እጅግ አደገኛ ሲሆን ስደተኞቹም በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚያልፉት።

መነሻቸውን ከምሥራቅ አፍሪካ ያደረጉ ስደተኞች ወደ የመን የሚያደርጉት ጉዞ ለዓመታት የቀጠለ ሲሆን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት ለመዝለቅ የሚሞክሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የመን ምቹ ተደርጋ ትታሰባለች።

ምንም እንኳ የመን ጭልጥ ባለ የእርስ በርስ ጦርነት የምትታመስ አገር ብትሆንም የኢኮኖሚ ስደተኞች አሁንም ወደዚያ ማቅናታቸውን እርግፍ አድርገው ለመተው አልፈቀዱም።