'ሴተኛ አዳሪ' በመባሏ የሚሊዮን ብር ካሳ

የቢራ ጠርሙሶች በጠረጴዛ ላይ ተደርድረው ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዊንፍሬድ ኒጆኪ ትባላለች። በናይሮቢ በባለ 5 ኮከቡ የኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል በመዝናናት ላይ ነበረች። ሴት ጓደኛዋ እስክትመጣ ቢራ አዝዛ እየተጎነጨች ሳለ ነው ጉድ የፈላው።

ሂቪሳሳ የተባለ የኬንያ የዜና ገጽ እንደዘገበው ከሆነ ተስተናጋጇ ብቻዋን ስለነበረችና ወንድ አብሯት ስላልነበረ ከሂሳቡ ዝርዝር የመግቢያ ክፍያ ትጠየቃለች።

ይህ ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ስትጠይቅ ከወንድ ጋር ስላልሆነች እንደሆነ ይነገራታል። ነገሩ ትክክል እንዳልሆነ በመከራከሯ በሆቴሉ አስተናባሪዎች ተገፍትራ እንድትወጣ ተደርጓል።

በወቅቱ "ሴተኛ አዳሪ" ተብላም ተሰድባ ነበር።

ከሆቴሉ መባረር ብቻም ሳይሆን የተከበረውን ሆቴል ሰላም አደፍርሳለች በሚል ለፖሊስ ተላልፋ በመሰጠቷ 2 ቀናትን በእስር ለማሳለፍ ተገዳ ነበር።

ፍርድ ቤት ታዲያ ለዚህ እንግልትና ለደረሰባት ያልተገባ ስድብ 3 ሚሊዮን ሽልንግ ወይም 30ሺህ ዶላር ካሳን ወስኖላታል። ይህ ወደ ብር ሲመነዘር ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ ነው።

የሆቴሉ አሳላፊዎች በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ በመመሥረትና ከወንድ ጋር እየተዝናናች ስላልነበረ ሴተኛ አዳሪ እንደሆነች ግምት እንደወሰዱ ተመልክቷል።

ካሳ የወሰኑላት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንዳሉት ድርጊቱ እጅግ አሳፋሪና ለተስተናጋጇ ውርደትን የሚያከናንብ ነበር ብለዋል። በዚህም የተነሳ ከሆቴሉ በተጨማሪ ዓቃቢ ሕግ አንድ ሚሊዮን ሺልንግ ካሳ እንዲከፍላት ይሁን ብለዋል።

ረዥም ዓመታትን በወሰደው በዚህ ፍርድ ተስተናጋጇ በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።