ካለሁበት 35፡ አቧራ እንደ ዝናብ ሲዘንብ አይቼ ስለማላውቅ ሁሌም ያስገርመኛል

አምለሰት ሃይሌ

የፎቶው ባለመብት, አምለሰት ሃይሌ

አምለሰት ሃይሌ እባላለው። ወደዚህ ሃገር ማለትም ኩዌት የመጣሁት በአጋጣሚ ነው። በጊዜው ልጅ ስለነበርኩ ስለ ስደት እንኳን የማውቀው ነገር አልነበረም።

በአንድ አጋጣሚ ከአስተማሪዬ ጋር መስማማት ስላልቻልኩኝ ለሳምንታት ትምህርት ቤት ሳልሄድ ቀረሁኝ።

በዚህ ጊዜ ለእረፍት ከኩዌት የመጣች አንዲት ልጅ አግኝቼ በቃ ወደ ኩዌት መሄድ እፈልጋለው ስላት ልጅ መሆኔን ተመልክታ አልተቀበለችኝም ነበር። እኔ ግን የሷን ምክር ከምንም ሳልቆጥር ልቤ የፈቀደውን ለማድረግ ወሰንኩኝ።

ኩዌትን ከኢትዮጵያ የተለየ የሚያደርጋት ሃብቷ ነው። እዚህ ያሉ ሰዎች ሲበዛ ሃብታሞች ናቸው። ኢትዮጵያ ግን የተፈጥሮ ሃብት ብቻ ነው ያላት።

እዚህ ሃገር ከሚያስገርመኝ ነገር አቧራው ነው። እንደ ዝናብ ነው የሚወርደው። ከኢትዮጵያ በጣም ይለያል። እኔ አቧራ እንደ ዝናብ ሲዘንብ አይቼ ስለማላውቅ ሁሌም ያስገርመኛል።

እዚህ ሃገር ስኖር ሁሌ የምናፍቀው ዓመት በዓልን ነው። ዓመት በዓል በደረስ ጊዜ ሁላችንም ተሰባስበን ነው የምናከብረው። ምክንያቱም ወደ ኋላ ወስዶ ያሳለፍነውን ማህበራዊ ህይወት፤ ልጅነታችን እና ኑሯችንን ስለሚያስታውሰን ነው።

ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ስለሆነ እንዲያመልጠኝ አልፈልግም።

የፎቶው ባለመብት, አምለሰት ሃይሌ

እዚህ ሃገር በጣም የማዘወትረው ከእንጉዳይ እና ጥራጥሬ የሚሰራ ምግብ ነው። ከመጠጥ ደግሞ ከፍራፍሬ እና ቅጠላ ቅጠል የሚሰራ ጭማቂ እወዳለሁ።

ከምኖርበት ከተማ የምወደው ባህሩን ነው። በመስኮት ወደ ውጪ ስመለከትም ይህን ባህር፣ መኪኖቹን እና ህንጻዎቹን ማየት ደስ ይለኛል። ለከተማዋ ልዩ ሞግስ ያጎናጽፏታል።

እንደ ትልቅ ነገር ልጠቅሰው የምችለው ችግር እስካሁን ባያጋጥመኝም፤ መጀመሪያ አካባቢ የሃገሩን ቋንቋ አለማወቄ ትልቅ እክል ሆኖብኝ ነበር።

አንድ አጋጣሚ ኖሮ ወደ ሃገሬ ብመለስ የምወዳት እና ሁሌም የምትናፍቀኝ ከተማ መቀሌ ሄጄ ማረፍ እፈልጋለው።