የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሥልጣናቸው ተነሱ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, ASHRAF SHAZLY

ጄኔራል አደም መሐመድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ።

ጀኔራል አደም መሃመድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተርነት ቦታን ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ነው የሚረከቡት። አቶ ጌታቸው አሰፋ ለበርካታ ዓመታት የሃገሪቱን የደህንነት መስሪያ ቤት በበላይነት የመሩ ሲሆን ስለእርሳቸው የአደባባይ ማንነት ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ለረጅም ዓመታት በቦታው ባገለገሉት ጀኔራል ሳሞራ የኑስ ቦታ ተተክተው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እንዲሆኑ ሾመዋቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ማዕረጋቸው ተነስቶ ከሠራዊቱ የተሰናበቱት ሜጄር ጀኔራል ዓለምእሸት ደግፌና ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ለሃገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነትን እውቅና በመስጠት ማዕረጋቸው እንዲመለስና ከሙሉ የጡረታ ጥቅማቸው ጋር ጡረታ እንዲወጡ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ገልፀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ጨምሮ እንደገለጸው፤ በተለያዩ የመንግሥት ሃላፊነቶች ላይ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት አቶ አባዱላ ገመዳ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ በጡረታ ተሰናብተዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤነት ተነስተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው በመሾም ለሁለት ወራት ያህል ቆይተዋል።