የአፍሪካ እግር ኳስ ቅሌት

Kwesi Nyantakyi reaches for piles of cash

በምዕራብ አፍሪካ እና ኬንያ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የእግር ኳስ ሃላፊዎች ከጨዋታ በፊት ገንዘብ ሲቀበሉ የሚያሳይ የምረመራ ዘገባ በቢቢሲ ከተላለፈ በኋላ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል።

ዘገባው የተሰራው በታዋቂው የጋና የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አረሜያው ሲሆን፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ማነቆዎችን በግልጽ ያሳየ ነው ተብሏል።

ሁለት አመት የፈጀው እና ለብዙ ሰአታት የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል የእግር ኳስ ዳኞች እና ሃላፊዎች ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው በፊት ገንዘብ ሲቀበሉ ያሳያል።

ይህ ቢቢሲ በተንቀሳቃሽ ምስሉ የተመለከተው ተግባር እና መሰል ድርጊቶች ተወዳጁን ስፖርት ለአመታት ወደኋላ ሲጎትቱት ቆይተዋል።

በምስሉ ላይ ሃላፊዎች ከጋና እና ማሊ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ በፊት ገንዘብ ሲቀበሉ ያሳያል። የተሰጣቸው ገንዘብ ውጤት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም በጨዋታው ጋና አሸናፊ ነበረች።

Image copyright Getty Images

ኬንያዊው ራንዤ ማርዋ የሩሲያውን አለም ዋንጫ ከሚመሩት የመስመር ዳኞች መካከል አንዱ ነው። በምስሉ ላይ 600 ዶላር ከአንድ ሰው ሲቀበል ይታያል።

የምርመራ ዘገባውን የሰራው ታዋቂው የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አረሜያው በሙያው የተካነ ነው። ብዙዎች ባይስማሙበትም መልኩ ምን እንደሚመስል ማንም ሰው አይቶት አያውቅም።

ጋዜጠኛው የተጠቀመው መንገድ ትክክል አይደለም ሲል የህግ ባለሙያ የሆነው ቻርለስ ቤንተም ይሞግታል።

''አንድን ሰው አጓጊ የሆነ ገንዘብ እንዲወስድ ማጓጓት እና ከወሰደ በኋላ ሙሰና ብሎ መጥራት ትክክል አይደለም''። ''በህጉ መሰረት ሰጪውም ተቀባዩም እኩል ጥፋተኛ ናቸው'' ይላል።

አናስ በበኩሉ ስላከናወነው ተግባር የራሱ መከራከሪያ አለው። በእያንዳንዱ ጨዋታ ሁሉንም ዳኞች የሚገዙ ህግ እና ደንቦች አሉ። የአፍሪካው ካፍም ሆነ አለማቀፉ ፊፋ፤ በየጊዜውለዳኞቻቸው ስለህጉ ስልጠና ይሰጣሉ የሚለው አናስ፤ ህጉን ማክበር ግዴታቸው ነው በማለት ይከራከራል።

''ማንም ኣላስገደዳቸውም፤ ገንዘቡን ሲቀበሉ የነበሩት ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ነው ሲል የጉዳዩን አሳሲቢነት ያብራራል።

በዘገባው ላይ የተካተቱትን ሶስት ሰዎች ቢቢሲ ለማነጋገር እና ሃሳባቸውን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከዘገባው በኋላ ኬንያዊው የመስመር ዳኛ ራንዤ ማርዋ ከሩሲያው የአለም ዋንጫ ራሱን እነዳገለለ ፊፋ ገልጿል።

የምርመራ ዘገባው የተሰራበት መንገድ ብዙ ጥያቄዎች ቢነሱበትም፤ የስፖርቱ አፍቃሪዎች ግን እግር ኳስ ምን ያህል እንደተበከለ አሳይቶናል እያሉ ነው።

ትናንት በወጡ መረጃዎች መሰረት የጋናው የእግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ገንዘብ ሲቀበሉ ያሚያሳየው ምስል ከተለቀቀ በኋላ፤ ጋና የእግር ኳስ ማህበሯን እንዳፈረሰች ተገልጿል።

Image copyright AFP

በምስሉ ላይ አንድ ሰው ባለሃብት በመምሰል እና የጋና እግር ኳስ ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍስ እንደሚፈልግ በመግለጽ ለክዌሲ ንያንታኪ 65 ሺህ ዶላር ሲሰጣቸው ይታያል።

የእግር ኳስ ማህበሩ ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የጋና መንግስት በተወዳጁ ስፖርት ላይ እየተፈጸሙ ባሉ ወንጀሎች ምክነያት የሃገሪቱን እግር ኳስ ማህበር ለማፍረስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዳስተላለፈ የመረጃ ሚኒስትሩ ሙስጣፋ አብዱል ሃሚድ ገልጸዋል።

ክዌሲ ንያንታኪ የጋና የእግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ፤ የካፍ ምክትል ፕሬዝዳነት እና የፊፋ ምክር ቤት አባል ናቸው።