ተማሪዎች ሞባይሎቻቸውን ሊነጠቁ ነው

ማክሮን ከደጋፊዎቻቸው ጋር የቡድን ፎቶ በመውሰድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዚዳንት ማክሮን ስልክ ከተማሪዎች እጅ እንዳይኖር ለማድረግ እንደሚሠሩ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል ገብተው ነበር

የፈረንሳይ ሕግ አውጪ ምክር ቤት የተንቀሳቃሽ ስልክን በትምህርት ቤቶች ውስጥ መጠቀመን የሚያግድ ረቂቅ አጸደቀ።

መንግሥት አዲሱ ሕግ ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ እንዲደርጉ ያበረታታል ብሎ ያምናል።

በተጨማሪም ረቂቁ "የኢንተርኔት ጉልቤዎችን" (cyber bullying) ተማሪዎች ላይ የሚያደርሱትን ዕለታዊ ጥቃት ያስቀራል ተብሏል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የልቅ ወሲብ ፊልሞችን በስልኮቻቸው እያጮለቁ የሚመለከቱ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችንም አደብ ያሲዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ተቺዎች በአንጻሩ የዚህን ሕግ ተግባራዊነት ይጠራጠራሉ። "እንዲሁ ለይስሙላ ካልሆነ ነገሩ ወደ መሬት ወርዶ አንደማይተገበር እናውቃለን" ይላሉ።

ይህ ረቂቅ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ዓመት ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ለደጋፊዎቻቸው ቃል የገቡትን ወደ ተግባር ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት እንደሆነ ተመልክቷል።

የፈረንሳይ ብሔራዊ ሸንጎ አባላትም ረቂቅ ሕጉን በሙሉ ድምጽ የደገፉት ሲሆን ትናንት ሐሙስ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መርተውታል።

ይህ ረቂቅ ተግባራዊ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎች በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን መጠቀም እንዳይችሉ ያግዳቸዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዤን ሜሽል ረቂቁን "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን" ሲሉ አሞካሽተውታል።

"ለቴክኖሎጂ ክፍት መሆን ማለት የመጣን ነገር ሁሉ መቀበል ማለት አይደለም" ሲሉ ለፈረንሳይ እንደራሴዎች ተናግረዋል።

በመጨረሻ ሰዓት በረቂቁ ላይ የተጨመረው አንቀጽ መምህራንም ቢሆን በትምህርት ክፍለ ጊዜ ስልኮቻቸውን መጠቀም እንዳይችሉ ዕቀባ ያደርጋል።

ወትሮም ቢኾን በመላው ፈረንሳይ ከሚገኙ 51 ሺህ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግማሾቹ በተማሪ ቤት ስልክ መጠቀምን ያግዳሉ። 7 ሺህ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀምን አይፈቅዱም።

ረቂቁ ከጸደቀ በአዲሱ የትምህርት ዓመት ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

በ2016 በተደረገ አንድ ጥናት ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 17 የሚሆኑ 10 ፈረንሳዊያን ተማሪዎች 8ቱ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ስልኮቻቸውን ይጎለጉላሉ።