''መፈተን የሚፈልጉትን እንፈትናለን..." ፍሬው ተገኔ (ዶ/ር)

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK/BAHIRDAR UNIVERSITY

የምስሉ መግለጫ,

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪዎች ተቃውሞ ለሦስተኛ ቀን ትናንት ቀጥሎ ውሏል። ከሦስተኛ ወደ አራተኛ ዓመት የሚሸጋገሩ የምህንድስና ተማሪዎች እንዲወስዱት ከተሰናዳ አዲስ አጠቃላይ ፈተና ጋር በተያያዘ ካለፈው መስከረም አንስቶ ሲንከባለል የቆየው የተማሪዎች ጥያቄ ለፈተና መቋረጥ ምክንያት ሆኗል።

ወደ ዩኒቨርስቲው የምህንድስና ተቋም ፤ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መግባታቸውንና ግጭቶች መከሰታቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ነግረውናል። ዩኒቨርስቲው በበኩሉ አጠቃላይ ፈተናው በትምህርት ሚኒስቴር የተተለመ አገር አቀፍ አቅጣጫ ነው ይላል።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሶስተኛ አመት የመካኒካል ምህንድስና ተማሪ፤ ግንቦት 30፥ 2010 (አርብ ምሽት አካባቢ)የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ተቋም የተሻሻለ ሁሉን አቀፍ የትምህርት ምዘና ህግ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ መለጠፉን ይናገራል።

''በማስታወቂያው መሰረት ሁሉን አቀፍ ፈተናው ከዚህ በፊት ሲሰራበት እንደነበረው ሳይሆን፤ በፈተናው ከ50 በመቶ በታች ያስመዘገበ ተማሪ ማለፍ እንደማይችልና ለአንድ አመት ትምህርት አቋርጦ ወደ ቤተሰብ መመለስ እንዳለበት ይገልጻል'' ብሏል ተማሪው።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሶስት አመታት በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት አቋርጠው እንደገና የጀመሩ፤ በፈተና ወድቀው ድጋሚ ተፈትነው ትምህርታቸውን የቀጠሉ ተማሪዎች ለፈተናው መቅረብ እንደማይችሉ አዲሱ ህግ ይገልጻል ሲል የሶስተኛ አመት የምህንድስና ተማሪው ይናገራል።

''በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የሶስተኛ አመት የምህንድስና ተማሪዎች፤ ሁሉን አቀፍ የሚባለውንና በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ለብዙ አመታት ሲሰጥ የነበረ ፈተና አንወስድም ብለው ጥያቄ አንስተዋል'' ያሉን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኔ ናቸው።

''ስርአተ ትምህርት በሰላማዊ ሰልፍ አይቀየርም፤ ለብዙ አመታት ስንጠቀምበት የነበረ ፈተና ነው''፤ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይ መንገድ ተማሪዎቻቸውን እየፈተኑ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ህጉ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መንገዶች ሲተገበር እንደነበር መረዳት ችለናል፤ ነገር ግን ህጉ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተላለፈ ነው የዶክተር ፍሬው አስተያየት ነው።

ፕሬዝዳንቱ ሲያክሉም ''መፈተን የሚፈልጉትን እንፈትናለን፤ ፈተናውን አንወስድም የሚሉትን ግን ልናስገድዳቸው አንችልም። ''ምርጫው የነሱ ነው'' ብለዋል።

ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ ግቢው አስተዳዳሪዎች በመሄድ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልጹ እንደዋሉ የነገረን ደግሞ ሌላኛው ያነጋገርነው ተማሪው ነው።

እሁድ ስራ ባለመኖሩ ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ ተማሪዎች በድጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበርና ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በየትምህርት ክፍላቸው ለማነጋገር ማስታወቂያ እንደለጠፈ ነግሮናል።

የተማሪዎች አድማው ማክሰኞም የቀጠለ ሲሆን፤ ዕሮብ ጠዋት ግን የክልሉ ልዩ ሃይሎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት ተማሪዎች ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ እንደጀመሩ ያነጋገርነው ተማሪ ገልጾልናል።

በመጨረሻም ከሰአት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኔ ተማሪዎችን ለማነጋገር በመወሰናቸው ነገሮች ትንሽ እንደተረጋጉ ተረድተናል።

ተማሪዎችም ህጉ አዲስ እንደሆነባቸውና በአመቱ መጀመሪያ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ እንዳልተገለጸላቸው ለፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን ተማሪዎች ገልጸውልናል።

ዶክተር ፍሬው ተገኔ በበኩላቸው ተማሪዎቹ ጋር መደማመጥ ስላልቻሉ ስብሰባው እንደተበተነ ነግረውናል።

እሮብ ጠዋት ግን ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው ንብረቶች ላይ ጉዳት ማድረስ በመጀመራቸው ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመነጋገር እርምጃ ለመውሰድ መገደዳቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲው የገባው የክልሉ ሰላም አስከባሪ ሃይል ተማሪዎችን እንደደበደበና ተማሪዎች ለማምለጥ ከግንብ ላይ ሲዘሉ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሌላኛው ያነጋገርነውና ማንነቱ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ተማሪ ነግሮናል።