አንስታይን ቻይኖችን "ቆሻሾች" ሲል ተሳድቧል

አልበር ኤንስታይን ጥቁር ሰሌዳ ላይ የሒሳብ ቀመር እየጻፈ

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY

አልበርት አንስታይን ቻይናዎችን "ቆሻሾች" ብሏቸዋል፤ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ስመጥር ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን ዘረኛና መጤ-ጠል እንደነበረ እየተዘገበ ነው።

ይህ የታወቀው በቅርቡ በታተመው የሳይንቲስቱ የገዛ የጉዞ ማስታወሻዎች ላይ ነው።

ይህ አቻ ያልተገኘለት ሳይንቲስት በዚህ ደረጃ ዘረኛና መጤ-ጠል (xenophobic) እንደነበር የሚያሳብቁ በርከት ያሉ አንቀጾች በማስታወሻው ላይ ሰፍረው መገኘታቸው ዓለምን ማነጋገር ይዟል።

እንደ ጎርጎሮሲያዊያን አቆጣጠር ከጥቅምት 1922 እስከ መጋቢት 1923 የተጻፉት የግል ማስታወሻዎቹ ኤንስታይን በኢስያ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ቆይታው ያስተዋላቸውን ነገሮች የከተበበት ነበር።

ጥቅልና ጅምላ ኮናኝ የሆኑት እነዚህ ማስታወሻዎቹ እሱ በተጓዘባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን ዘረኛ በሆነ መንገድ ይመለከታቸው እንደነበር አሳብቀዋል።

ለምሳሌ ቻይናዎችን "የማይደክማቸው ሠራተኞች፣ ቆሻሾችና ደነዝ ሕዝቦች" ሲል በማስታወሻው ገልጧቸዋል።

አንስታይን በመጨረሻ ሕይወቱ አሜሪካ ውስጥ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች እንደነበር ሲታሰብ ከእነዚህ አስተያየቶቹ ጋር እሱን ለማስታረቅ ከባድ ሆኗል። እንዴትስ በዚህ ደረጃ ዘረኛ ሊሆን ቻለ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሆኗል።

ዘረኝነትን አንስታይን "የነጮች በሽታ" ሲል ነበር የሚጠራው።

የኤንስታይን ማስታወሻዎች ራሳቸውን ችለው በመድበል መልክ በእንግሊዝኛ ሲታተሙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ኤንስታይን በዚያ ዘመን ከስፔን ተነስቶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከዚያም በሲሪላንካ ወደ ቻይናና ጃፓን ተጉዞ ነበር።

በግል ማስታወሻው ስለ ግብጾች እና የሲሪላንካ ሕዝቦችም በተመሳሳይ ሁኔታ መልካም ያልሆኑና ከርሱ የማይጠበቁ አስተያየቶችን መስጠቱን ከመጽሐፉ መደራት ይቻላል።

በሌላ አንቀጽ ስለ ቻይና ሕጻናት ያልተገባ አስተያየት ሲሰጥ "ድንዙዝና ምንም የልጅነት ፈንጠዚያ እንኳ ያልፈጠረባቸው፣ እንዲሁም ፈዛዞች" ብሏቸዋል።

ይህም ሳያንሰው ቻይኖች "እንደ በግ በጅምላ የሚነዱ፣ ሰው ሰው የማይሸቱ ሮቦቶች" ብሏቸዋል።

"ሴቱን ከወንዱ እንኳ ለመለየት የሚያስቸገር ሕዝብ" ሲልም ተሳልቋል።

እጅግ ሲከበር የኖረው ይህ ጎምቱ ሳይንቲስት በናዚዎች ላይ ከሚደርሰው ጭቆና በመሸሽ ወደ አሜሪካ ምድር የገባው በ1933 ነበር።

በወቅቱ በጥቁሮችና በነጮች መሐል የነበረውን መከፋፈል ሲመለከት እጅግ መደንገጡ ይነገራል። ጥቁሮችና ነጮች የተለያየ ትምህርት ቤትና የተለያየ ሲኒማ ቤት እንደሚሄዱ ባየ ጊዜም ሐዘን ተሰምቶት ነበር።

ይህን ያልተገባና ኋላቀር ዘረኝነት ለመቃወምም በወቅቱ የነበረውን ከጥቁርና ከነጭ የተወለዱ ዜጎች ያቋቋሙት የብሔራዊ ባለቀለም ዜጎች ማኅበርን ተቀላቅሎ ነበር።

እንዲያውም በንግግሮቹ ውስጥ አሜሪካ በጥቁሮች ላይ የምታደርሰውን መገለል ጀርመን በነበረበት ወቅት በአይሁዶች ላይ ከሚደርሰው ጭቆና ተመሳሳይ ነው ሲል ይናገር ነበር።

ስለ አንጻራዊ ለውጥ Relativity theory አብዝቶ የተጨነቀውና ለዓለም አዲስ እሳቤን ያበረከተው ይህ ጉምቱ ሳይንቲስት አንጻራዊ ዘረኝነቱን በሂደት አራግፎት ይሆን?