21ኛው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ በድምቀት ተጀመረ

የዓለም ዋንጫ

ሃያ አንደኛው የአለም ዋንጫ በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ዛሬ በደማቅ ስነስርአት ተጀምሯል። 32 ሃገራት በሚሳተፉበት ይህ ተወዳጅ ውድድር ሩሲያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ አድርጋለች።

81 ሺህ ተመልካቾች ማስተናገድ በሚችለውና ከአስራ ሁለቱም ስታዲየሞች ትልቁ የሆነው ሉዥኒኪያ ሰታዲየም ደማቁን የመክፈቻ ስነስርአት አስተናግዷል። በታዋቂው እንግሊዛዊ አቀንቃኝ ሮቢ ዊሊያምስ ሙዚቃ የተጀመረው መክፈቻው፤ የሩሲያን ባህላዊ እና ታሪካዊ ትውፊቶችን ለተመልካቾች ያሳየ ነበረ።

የሰላሳ ሁለቱም ተካፋይ ሃገራትን ባንዲራ የለበሱ የበአሉ ተካፋዮች፤ የእግር ኳስን ሰላማዊነት የሚያሳዩ የተለያዩ ትዕይንቶችን አቅርበዋል። በስታዲየሙ በስተግራ በኩል የተካፋይ ሃገራት ባንዲራዎች የተደረደሩበት መንገድ የብዙ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ ነበር።

ከመላው ዓለም ብዙ ሚሊየኖች በተከታተሉት የመክፈቻ ስነስርአት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በስታዲየሙ ለተሰበሰቡት የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እንኳን ወደ ሩሲያ በደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን አድርገዋል።

ሌላኛው በስታዲየሙ የነበሩት የክብር እንግዳ፤ የአለማቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኖ ኢንፋንቲኖ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በሩሲያኛ እና በአረብኛ አስተላልፈዋል።

ለሚቀጥሉት 30 ቀናት ሩሲያ በእግር ኳስ ትወረራለች፤ መላው አለም ደግሞ ከሩሲያ በኩል በእግር ኳስ ይወረራል ብለዋል።

የመክፈቻ ስነስርአቱን ያስተናገደውና የዋንቻ ጨዋታውን የሚየዓስተናግደው ሉዥኒኪያ ስታዲየም ከክረምቱ ውድድር በኋላ የዓለም ዋንጫ፣ የአውሮፓ ዋንጫ እና የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎችን በማስተናገድ በዓለማችን አምስተኛው ይሆናል።