የወባ በሽታ ያለ ደም ምርመራ ሊታወቅ ነው

የፈጠራው ባለቤት ጊታ Image copyright AFRICA PROOF
አጭር የምስል መግለጫ የፈጠራው ባለቤት ጊታ

አንድ ኡጋንዳዊ የፈጠራ ባለሙያ የወባ በሽታን ያለደመ ናሙና የሚመረምር መሳሪያ በመፍጠሩ ትልቅ ሽልማት አሸነፈ።

የ24 ዓመቱ ወጣት ጊታ ሮያል አካዳሚ ኦፍ ኤንጂነሪንግ ከተባለ ተቋም፤ የበሽተኛው ጣት ላይ ቀይ መብራት በማብራት ብቻ የወባ በሽታ መኖር አለመኖሩን የሚመረምር መሳሪያ በመፍጠሩ የአፍሪካ ተሸላሚ ሆኗል።

ውድድሩን ያሸነፈው ጊታ የ25 ሺህ ዶላር ሽልማትን ሲሆን፤ በአዲሱ መሳሪያ የተደረገው ምርመራ ውጤት ከደቂቃ በኋላ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ማየት እንደሚቻል ገልጿል።

ኡጋንዳዊው የሥራ ፈጣሪ የወባ ምርመራ ለማድረግ ወደ ህክምና ቦታ ሄዶ በጊዜው ደሙን የሚመረምረው መሳሪያ ውጤቱን ማሳየት ስላልቻለ፤ ይህንን ''ማቲባቡ'' የተባለውን የፈጠራ ውጤት ለመስራት እንደተነሳሳ ተናግሯል።

በኡጋንዳ የወባ በሽታ ገዳይ ከሚባሉት አንዱ ሲሆን፤ የመሳሪያው ፈጣሪ ጊታ ደሙ አራት ጊዜ ተመርምሮ ነበር ውጤቱን ማወቅ የቻለው።

የ'ማቲባቡ' ፈጠራ ቡድን አባል የሆነው ሴኪቶ እንደሚለው በኮምፒዩተር ምህንድስና ያገኘነውን እውቀት ለምን አንድን ሰው ደሙ ሳይፈስ ወባን ለመመርመር አንጠቀምበትም በማለት ጊታ ሃሳቡን እንዳቀረበ ይናገራል።

ሽልማቱን ለመስጠት በነበረው ውድድር የተሳተፉት አንደኛው ዳኛ ''ምህንድስና የህይወት ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን ማሳያ ነው'' ብለዋል።

'ማቲባቡ' በስዋሂሊ ቋንቋ ህክምና ማለት ሲሆን፤ በሽታውን ለመመርምር የግድ የህክምና ባለሙያ አያስፈልግም።

መሳሪያው የነጭ ደም ሴሎች እንቅስቃሴንና የደም ቀለምን በመመልከት ታካሚው በበሽታው መያዝ አልያም አለመያዙን ያመለክታል።

ጊታ እና የቡድን አጋሮቹ የመሳሪያው መፈጠር ለአፍሪካ ፈተና የሆነውን የወባ በሽታ ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ተስፋ አድርገዋል።

የወባ መመርመሪያ መሳሪያው ወደ ገበያ ከመቅረቡ በፊት ብዙ የደረጃ ምዘና ፈተናዎችን ማለፍ እንዳለበት ጨምረው ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች