በጎርፍ አደጋ ወቅት የሚደረጉ አምስት ጥንቃቄዎች

በጎርፍ አደጋ ወቅት የሚደረጉ አምስት ጥንቃቄዎች Image copyright AFP

በያዝነው ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሞተዋል። ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መቆጣጠር ወይም መቀነስ ይቻላል።

በአሁኑ ሰዓት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ዝናባማ የሚባለው የክረምት ወቅት ቀደም ብሎ የጀመረ ይመስላል። ከዚህ ዝናብ ጋር ተያይዞ የዝናብ ውሃው ወደ መሬት ቶሎ መዝለቅ ካልቻለ ወይም የተለዩ መውረጃዎች ካልተሰሩለት ጎርፍ ሊከሰት ይችላል።

ጎርፍ ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ጉዳት ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ የሚከተሉት አምስጥ ነጥቦች ወሳኝነት አላቸው።

1. ማዳሪያዎችና ሌሎች ከረጢቶችን በአሸዋ ሞልቶ ከበር ደጃፍ ላይ መደርደር

እንደ አማራጭ ጎርፍ ወደ ቤት እንዳይገባ፤ በቤት ዙሪያ የውኀ መፍሰሻ ቦይ ወይንም ጉድጓድ መቆፈር ይችላሉ። በርና መስኮቶችን በደንብ መዝጋቶን አይዘንጉ።

2. እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ያለበትን ሁኔታ ያጣሩ

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ያለበትን ሁኔታ ማወቅ ሌሎች ጥንቃቄዎችን በተረጋጋ መንፈስ ለማድረግ ይጠቅማል። የታሰሩ የቤት እንስሳት ካሉ መፍታት እንዳይረሱ።

3. በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ማንኛውም መጠቀሚያዎችን ከሶኬት ላይ ይንቀሉ

ከጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ ስዎች ሊጠነቀቁት የሚገባ ነገር የኤሌክትሪክ አደጋ ነው። ከቤት ውስጥ ባለፈ በውጪም ቢሆን የወደቁ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ካሉጥንቃቄ ያድርጉ። የተቆፈሩ ጉድጓዶች ካሉ ሰዎች ገብተው እነዳይወድቁ በደንብ ይክደኗቸው።

4.ቆሻሻ ወደ ውጪ እንዳይወጣ መጸዳጃ ቤቶችን በደንብ ይዝጉ

እንደ ጸረ ተባይ እና የመሬት ማዳበሪያ ያሉ መርዝነት ያላቸው ነገሮችን ጎርፉ የማይደርስበት ከፍ ወዳለ ቦታ ያስቀምጧቸው። ምክንያቱም የተበከለ ውሃ ሌላ ተጨማሪ በሽታ ይዞ ሊመጣ ይችላል።

5. ከፍ ወዳለ ቦታ ይሂዱ፤ አልያም የቤተትዎ ጣራ ላይ ይውጡ

የጎርፍ አደጋ በሚያጋጥሞት ጊዜ ቤት ውስጥ ሆነው ራሶን መከላከል ካልቻሉ፤ ወደ ጣራ ላይ ወይንም ከፍ ወዳለ ቦታ ይውጡ። በጎርፍ ውስጥ መራመድ ደግሞ አይመከርም።