ሊዮኔል ሜሲን ምን ነካው?

ሊዮኔል ሜሲ Image copyright Getty Images

አርጀንቲና በክሮሺያ 3-0 ከተሸነፈች በኋላ ሊዮኔል ሜሲ እጅግ አዝኖ ወደ መልበሻ ክፍል ሲገባ የሚያሳይ ምስል በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ከታዩ አሳዛኝ አጋጣሚዎች አንዱ ሆኗል።

በሁለቱም የምድብ ጨዋታዎች ምንም ጎል ያላስጠረው ሜሲ፤ ለጎል የሚሆን ኳስ እንኳን አመቻችቶ ማቀበል አልቻለም። እንደውም ከአይስላንድ በነበራቸው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ አርጀንቲና ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጎል መቀየር ሳይችል ቀርቷል።

30ኛ ዓመቱን የደፈነው ሜሲ ከዚህኛው ውድድር በኋላ ሌላ የዓለም ዋንጫ እንደሚጫወት የሚጠበቅ ሲሆን፤ የእግር ኳስ ተንታኞች ግን ለሃገሩ ትልቅ ነገር ለማበርከት ይህ ዓመት ብቻ ነው ያለው ይላሉ።

በ2022ቱ የዓለም ዋንጫ 34 ዓመት የሚሞላው ሜሲ በዚያ ዕድሜው ለሃገሩ ብዙ ነገር ያበረክታል ብሎ መገመት የማይቻል ነው የሚያቀርቡት መከራከሪያ ነው።

በክለቡ ባርሴሎናም ቢሆን የሃገር ውስጥ ሁለት ዋንጫዎችን ከማንሳቱ ውጪ፤ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ስኬታማ መሆን አልቻለም። ተቀናቃኛቸው ሪያል ማድሪድ ለተከታታይ ሶስተኛ ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ሲሆን ማየት ደግሞ ግድ ሆኖበታል።

ሜሲ ምን አጋጥሞት ነው ታድያ ይህ ዓመት እጅግ ከባድ የሆነበት? ሃገሩንስ በሩሲያው የአለም ዋንጫ ለምን መርዳት አልቻለም?

Image copyright Getty

1) የአካል ብቃቱ ተዳክሟል

በፈረንጆቹ 2017/18 የውድድር ዘመን ብቻ ለቡድኑ 54 ጨዋታዎችን የተጫወተ ሲሆን፤ ከዚህ በላይ ጨዋታዎችን ያደረገው ገና የ25 ዓመት ወጣት እያለ ነበር።

'ትራንስፈር ማርኬት' ከተባለው ድህረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ሜሲ 4468 ደቂቃዎችን የተጫወተ ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ባደረጋቸው ጨዋታዎች 82 ደቂቃዎች በሜዳ ላይ ቆይቷል።

ነገር ግን በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆኖ እንኳን ለባርሴሎና 45 ግቦችን አስቆጥሮ፤ 18 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል።

2) ተደጋጋሚ ጉዳት

ሚያዚያ 2018 ላይ አንድ የአርጀንቲና ጋዜጣ ከታማኝ የብሔራዊ ቡድን ምንጭ አገኘሁት ብሎ ይዞት እንደወጣው መረጃ ከሆነ፤ ሜሲ በቀኝ እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህም ምክንያት እንደ ድሮው ፈጣን እና ያልተጠበቁ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አልቻለም።

የጉዳቱ ዜና ይፋ የሆነው ሃገሩ አርጀንቲና ከውድድሩ በፊት ባደረገቻቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ወቅት ነበር። እንደውም አርጀንቲና በስፔን ስድስት ለአንድ ስትሸነፍ ተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖ ነበር የተመለከተው።

3) በዚህኛው የለም ዋንጫ አርጀንቲና ሩ ቡድን ይዛ አልመጣችም

አርጀንቲና ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በነበራት የደቡብ አሜሪካ የማጠሪያ ውድድር እጅጉን ተቸግራ ነበር ለማለፍ የቻለችው። በማጣሪያ ጨዋታዎቹ ሜሲ 8 ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ቢጨርስም፤ የብሔራዊ ቡድኑ ደካማ እንቅስቃሴ ግን ከትችት አልዳነም።

በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ለፍፋሜ ደርሳ በተጨማሪ ሰዓት በተቆጠረባት ግብ በጀርመን መሸነፏ የሚታወስ ነው። ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያሸነፈችው በ1986ቱ ነበር።

ከ1993 በኋላ የደቡብ አሜሪካ ውድድር የሆነውን 'ኮፓ አሜሪካ' እንኳን ማሸነፍ ያልቻሉት አርጀንቲናዎች፤ በ2004 እና 2008 ኦሎምፒክ ላይ ያነሷቸው ዋንጫዎች ብቻ አንደ ትልቅ ስኬት ይቆጠርላቸዋል።

Image copyright Getty

4) የሮናልዶ አስገራሚ ብቃት

በሩስያው የዓለም ዋንጫ የሁልጊዜም ተቀናቃኙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አስደናቂ ብቃት ላይ መገኘት ሜሲ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲደርስበት አድርጓል።

ሮናልዶ ሃገሩ ፖርቹጋል ከስፔን በነበራት የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ሶስት ጎሎችን አስቆጥሮ ሃገሩን ከመሸነፍ ያዳነ ሲሆን፤ ከሞሮኮ በነበራቸው ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል በጭንቅላቱ አስቆጥሮ ሃገሩ ከምድቧ ለማለፍ የምታደርገውን ጉዞ አግዟል።

ሮናልዶን የሚያቆመው ያለ አይመስልም፤ በሌላ በኩል ሜሲ ደግሞ አርጀንቲና ከአይስላንድ በነበራት ጨዋታ ፍጹም ቅጣት ምት መሳቱ የእግር ኳስ ተንታኞች ሜሲ ምን ነካው? እንዲሉ አስገድዷቸዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ሮናልዶ በ2016ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ሃገሩን ለድል ማብቃቱ፤ አርጀንቲናውያን ሜሲስ መቼ ነው ለሃገሩ የማይረሳ ነገር ሚያደርገው? እያሉ እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ ተጫዋቹ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰበት ይገኛል።

የብዙዎች ፍርሃት ከወዲሁ አርጀንቲና ከምድቧ ተሰናብታ ሜሲ የአለም ዋንጫ ተመልካች እነዳይሆን ነው።