የቱርክ ምርጫ፡ ኤርዶጋን ፕሬዝዳንታዊውን ምርጫ አሸነፉ

የኤርዶጋን እና የኤኬ ፓርቲ ደጋፊዎቸ ደስታቸውን ለመግለጽ በኢስታንቡል አደባባይ ወጥተዋል። Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የኤርዶጋን እና የኤኬ ፓርቲ ደጋፊዎቸ ደስታቸውን ለመግለጽ በኢስታንቡል አደባባይ ታይተዋል።

ለበርካታ ዓመታት የቱርክን ፖለቲካ ተቆጣጠረውት የቆዩት ረሲፕ ጣየር ኤርዶጋን ፕሬዝደንታዊ ምርጫውን በማሸነፍ ለአምስት ዓመታት ሥልጣን ላይ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል።

የምርጫ ሃላፊው ሳዲ ጉቬን ''ፕሬዝደንቱ አብላጫውን ድምጽ አግኝተዋል'' ብለዋል።

ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ኤርዶጋን 53 በመቶ ተቀናቃኛቸው ሙሃሬም ኢንስ ደግሞ 31 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ዘግቧል።

ተቃዋሚ ፓርቲው መሸነፉን እስካሁን ባያምንም የምርጫው ውጤት ምንም ቢሆን ምን ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እቀጥልበታለው ብሏል።

ይፋዊ የሆነው የምርጫ ውጤት የፊታቸውን አርብ የሚገለጽ ይሆናል።

ምርጫው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበት ምርጫ ነው ተብሏል።

የ64 ዓመቱ ኤርዶጋን ከፓርቲያቸው መቀመጫ አንካራ ከተማ ምርጫውን ማሸነፋቸውን የገለጹ ሲሆን በመግለጫቸውም ''የዚህ ምርጫ አሸናፊ 81 ሚሊዮን የአገሬ ዜጎች ናቸው'' ብለዋል።

የቱርክ ሕገ-መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት በህዝበ ውሳኔ የተሻሻ ሲሆን ይህም ምርጫውን ላሽነፉት ኤርዶጋን ፖለቲካዊ የሥልጣን ኃይልን ይጨምራል።

በዚህም መሰረት ኤርዶጋን አስቸኳይ የጊዜ አዋጅን ማወጅ፣ የህዝብ እንደራሴዎችን፣ ሚንስትሮችን እና ምክትል ፕሬዝደንቶችን በቀጥታ መሾም ይችላሉ። እንዲሁም በአገሪቱ የህግ ስርዓት ላይ ጣልቃ መግባትን ይፋቅድላቸዋል።

በርካቶች ግን የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ለኤርዶጋን ከፍተኛ ስልጣን በመስጠት አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጣር ተጠያቂ የሚያደርግ ስርዓት እንዳይኖር ያደርጋል ይላሉ።

ኤርዶጋን ሕገ-መንግሥቱ የሚሰጣቸው ሥልጣን፤ የቱርክን ኢኮኖሚ ለማጠናከር እና በአገሪቱ ደቡብ ምስራቅ የሚንቀሳቀሰውን የኩርድ አማጺያንን ለመደምሰስ ያስችለኛል ይላሉ።

አሸናፊነታቸውን ባወጁበት ንግግራቸው ''አሸባሪ ቡድኖችን እዋጋለሁ፣ የሶሪያንም ምድር ነጻ በማውጣት ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እሰራለሁ'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ኤርዶጋን እአአ በ2004 ፕሬዝዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ለ11 ዓመታት ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ቆይተዋል። በተሻሻለው ሕገ-መንግሥት መሰረት አሁን የያዙት የስልጣን ዙር ሲጠናቀቅ ለሶስተኛ ዙር መወዳደር ይችላሉ፤ በዚህም እሰከ 2028 ድረስ ስልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች