በሳዑዲ አረቢያ ሴቶች ላይ ተጥሎ የነበረው የማሽከርከር እገዳ ተነሳ

ሀናን ኢስካን ለመጀመርያ ጊዜ መኪና በማሽከርከሯ ቤተሰቦቿ ደስታቸውን እየገለጹላት ነው። Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሀናን ኢስካን ለመጀመርያ ጊዜ መኪና በማሽከርከሯ ቤተሰቦቿ ደስታቸውን እየገለጹላት ነው።

ከአስርት ዓመታት በፊት የወጣውና ሴቶች እንዳያሽከረክሩ የሚያግደው ሕግ መነሳቱን ተከትሎ የሳዑዲ ሴቶች የማሽከርከር ፈቃድ አግኝተዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ከዓለማችን ለሴቶች የማሽከርከር ፈቃድ የማትሰጥ ብቸኛዋ አገር የነበረች ሲሆን በዚህም ምክንያት ሴቶች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የወንዶችን መልካም ፍቃድ ጠባቂ ሆነው ቆይተዋል።

በዚህም ሳቢያ ሾፌር አሊያም መኪና ሊያሽከረክር የሚችል ወንድ ዘመድ ለመቅጠር ይገደዱ ነበር።

በአገሪቱ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሴቶች የማሽከርከር ፈቃድ እንዲያገኙ ለዓመታት ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳስታወቀው በሴቶች የማሽከርከር መብት ስሟ ቀድሞ የሚነሳውን ሎጃኢን ሃትሎልን ጨምሮ በትንሹ ስምንት የሴቶች መብት ተሟጋቾች ተይዘው፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው ረዘም ላለ ጊዜ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

የማሽከርከር እገዳው ሕግ በአውሮፓውያኑ መስከረም ወር የተሻሻለ ሲሆን በያዝነው ወር መጀመሪያ ሕጋዊ የማሽከርከር ፈቃድ ለዐስር ሴቶች መሰጠት ተጀምሮ ነበር። ስለሆነም ሴቶች በወንዶች ሞግዚትነት የሚቆዩበትን ሕግ እንዳበቃለት ተነግሯል።

"ይህ ለሳዑዲ ሴቶች ታሪካዊ አጋጣሚ ነው" ሲሉ የሳዑዲ ቴሌቪዥን አቅራቢ ሳዲቃ አል-ዶሳሪ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

የ ሃያ አንድ ዓመቷ የሕክምና ተማሪ ሀቱን ቢን ዳኪል በበኩሏ ለረጂም ሰዓት ቆመን ሾፌር የምንጠብቅበት ሰዓት አክትሟል ፤ ከዚህ በኋላ ወንዶች አያስፈልጉንም " በማለት አጋጣሚውን ገልፀዋለች።