የፊሊፒንሱ መሪ ፈጣሪን ተሳደቡ

ዲቶርቴ የጦር መሣሪያ ይዘው ይታያሉ Image copyright Reuters

በአወዛጋቢነታቸው ዓለም የሚያውቃቸው የፊሊፒንሱ መሪ ዱቴርቴ አሁን ደግሞ አምላክን ተዳፍረዋል።

በቴሌቪዥን ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የአዳምና የሄዋንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ካንኳሰሱ በኋላ የሰው ልጅ ሐጥያተኛ ነው የሚለውን ትርክት ተሳልቀውበታል።

ዱቴርቴ ወትሮም ተቃዋሚዎቻቸውን በመወረፍ የሚታወቁ መሪ ናቸው።

የርሳቸውን ንግግር ተከትሎ ቤተክርስቲያንና ዜጎቻቸው ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን የርሳቸው ጽሕፈት ግን ይህ የርሳቸው የግል አመለካት እንደሆነ በመግለጽ የተቆጣን ሕዝብ ለማረጋጋት ሞክሯል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዚዳንቱ በሌላ ንግግራቸው የአገሪቱን ዕውቅ ጳጳስ ተሳድበው አገር ጉድ ብሎ ነበር።

ከዚህም ባሻገር ሴቶችን የሚያሳንሱና የሚያዋርዱ ንግግሮችን በመናገር ይተቻሉ።

ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር አዳምና ሄዋን ከገነት የተባረሩበትን መንገድ በማውሳት በዚያ ታሪክ ለመሳለቅ ሞክረዋል።

በተለይም ውርስ ሐጥያት በሚባለው መንፈሳዊ ሐሳብ ላይ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ "ምን ዓይነት ሃይማኖት ነው ይሄ? እኔ እንዲህ አይነት ነገር አልቀበልም' ብለዋል።

አርቱር ባስተስ የተባሉ የአንድ አድባር ቄስ ዲቶርቴን "ቀወስ" ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

ፊሊፒንስ ከ90 በመቶ በላይ ዜጎቿ ጥብቅ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች