የትናንትናዋ እለት- በኢትዮ ኤርትራ ግጭት ቤተሰባቸው ለተለያየ?

ዮናስ አብርሃምና ሳሚያ እዮብ Image copyright BBC/yeberana lijoch

እርሱ ኢትዮጵያ ፤ ወንድሙም ኤርትራ ውስጥ ጋዜጠኛ ነበር።

ሁለቱ ወንድማማቾች ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃምና ጋዜጠኛ በረከት አብርሃም ለተለያየ አገር የመንግስት ስርዓት ጋዜጠኛ ሆነውአንዳቸው ሻእቢያ ፤ሌላኛቸው ደግሞ ወያኔ እያሉ ፅንፍ ለፅንፍ ሆነው ሲዘግቡ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ጋዜጠኛና ደራሲ ዮናስ አብርሃም ተውልዶ ያደገው ኢትዮጵያ ነው።

በሁለቱ አገራት ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ ይሰራ ስለነበር ከርሱ ውጭ ያሉ የቤተሰቡ አባላት ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ እርሱ ኢትዮጵያ ተነጥሎ ኢትዮጵያ ቀርቷል ።

"እናቴ በአውቶብስ ተሳፍራ ስትሄድ ተደብቄ አያት ነበር" ሲል ከቤተሰቡ ጋር የተለያየበትን ጊዜ ያስታውሳል።

ላለፉት ሃያ ዓመታት ከቤተሰቦቹ ጋር በዓይነ ስጋ እንዳልተገናኘ የሚናገረው ዮናስ በቅርቡ በረከትን ጨምሮ ሌሎች ወንድሞቹ በድንበር አካባቢ ጠፍተው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።ይሁን እንጂ በተወለዱበት አገር ስደተኛ እንደሆኑ ይናገራል።

"የአገራቱ ድንበር ያለው ዛላምበሳ፣ ባድመና የመሳሳሉት የድንበር መስመሮች ላይ ብቻ አይደለም ፤ የእናታችን ማህፀን ውስጥም ድንበሩ አለ ማለት ነው" ሲል የሁለቱ አገራት ቁርሾ ያስከተለውን ጣጣ ይናገራል።

አሁን ሁለቱ አገራት የጀመሩት የሰላም ግንኙነት ሃዘን የሚያበቃበት፣ አዲስ ተስፋ የሚመጣበትና አገራቱንና ህዝቡን የሚጠቅም እንደሚሆን ተስፋ አለው። "ተስፋ ቆርጨ ስለነበር ግንኙነቱ ይበልጥ አስደናቂ ሆኖብኛል" ብሏል።

ሳሚያ እዮብ የተወለደችው አስመራ ነው። ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ነው። ኢትዮጵያዊቷ ሳሚያን የሁለቱ አገራት ጠብ ከአባቷ ጋር ለያይቷታል። ከ 1993 ዓ.ም ጀምሮ በምንም ዓይነት አጋጣሚ ከአባቷና ቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝታ አታውቅም። አሁን ሁለቱ አገራት የጀመሩት የሰላም ግንኙነት አባቷን ለማየት ተስፋ እንደሰጣት ትናገራለች፤ ትንሿ ሮማ የምትባለውን ኤርትራን መጎብኘትም ትሻለች።

ከኤርትራ ለመጣው ከፍተኛ ልዑካን አቀባበል ለማድረግ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኘችው ድምፃዊት ፀደኒያ ገብረ ማርቆስም ሁለቱ አገራት የጀመሩት የዕርቅ ጉዞ ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነ ትገልፃለች።

"ከዚህ በኋላ ምን እንደሚሆን ባላውቅም፤ ጥሩ ነገር ይፈጠራል ብየ አስባለሁ፤ ግንኙነቱም መልካም ይሆናል" ትላለች።

ቀኑን በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አትሌት ስለሺ ስህን ዛሬ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ነገር በጣም ደስ የሚል እንደነበር ይገልፃል።

"አንድ ቀን ጠንካራ መሪ ሲፈጠር ሁለቱን አገራት አንድ ያደርጋል" ሚል ተስፋ እንደነበረውም ይናገራል።

"ይህ ቀን የሰላም ቀን ብዬ አሰብኩት" ያለን ደግሞ አትሌት ገብረ እግዚያብሔር ገ/ማሪያም ነው። አቀባበል ለማድረግ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ረጅም ሰዓት እንደቆየ የሚናገረው አትሌቱ መዘግየታቸው ስጋት ፈጥሮበት እንደነበርና ልዑካኑን የያዘው አውሮፕላን ሲያርፍ ግን ሰላም ከዛሬ ጀምሮ እውን ሆኗል ማለት ነው የሚል ስሜት እንደተሰማው ገልፆልናል።

ሌሎች ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጭዎችም ሰላም እንደሚፈጠር ይጠብቃሉ።

ከዚህ በፊት በነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር ስምምነት አለመደረጉን ገልፀው አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር የጀመሯቸው መልካም ግንኙነቶች ዕርቅ ላይ እንደሚያደርስ ተስፋቸውን የገለፁም አሉ።

"ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንን እንወዳለን፤ እነሱም እንደሚወዱን ተስፋ አደርጋለሁ። ህዝብ ለህዝብ ቅርርብን ለመፍጠር መንግስታቱ ጠንክረው ቢሰሩ ደስ ይለኛል፤ እኔም ወደ አስመራ መሄድ እፈልጋለሁ" ብላች አንድ አስተያየት ሰጭም።

የአገራቱ ስምምነት ኢትዮጵያን ወደብ ተጠቃሚ ያደርጋታል፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል ጉልህ ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀውልናል።

ተያያዥ ርዕሶች