ሞዴሏ በእየሩሳሌም የተነሳችው ፎቶ ቁጣን ቀሰቀሰ

የእለት ተዕለት ሕይወት በእየሩሳሌም Image copyright NurPhoto

ቤልጅየማዊቷ አርቲስት በእስራኤል "እጅግ የተቀደሰ" በሚባል ሥፍራ የተነሳችው የዕርቃን ፎቶ ውግዘትን እያስከተለባት ነው።

ማሪሳ ፔፔን የእርቃን ፎቶውን የተነሳችው ቅዱስ በሚባለውና በምዕራብ እየሩሳሌም በሚገኘው "የአይሁዳዊያን ግድግዳ" ላይ ተንፈላሳ በመቀመጥ ነው።

አንድ የአይሁድ እምነት አባት ድርጊቱን "አስነዋሪና ስርየትን የሚያስጠይቅ የሀጥያት ተግባር" ብለውታል።

ወትሮም ቢሆን ሞዴሏ በድረገጽ የምታዛምታቸው የዕርቃን ፎቶዎቿ ከውዝግብ ርቀው አያውቁም።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ በግብጽ አንድ ጥንታዊ ቤተመቅደስ እርቃኗን ፎቶ ከተነሳች ወዲህ በቁጥጥር ሥር ውላ ነበር።

የሞዴሏ የሕይወት ዘይቤዋና ፍልስፍናዋ "በእርቃን ውስጥ ነጻነትን ማወጅ" የሚል ነው።

"ሰዎች ባይታወቃቸውም ጭምብል ውስጥ ናቸው። ያን መግፈፍ ያስፈልጋል" ትላለች።

የሰው ልጆች ይህንን ጭምብላቸውን ቀዳደው ባሕር ውስጥ እስካልጨመሩት ድረስ ነጻነት ውሸት ነው የሚል ፍልስፍናን ታራምዳለች።

የዕርቃን ሞዴሏ ፎቶ ከፍ ያለ ቁጣን የቀሰቀሰው ከሰሞኑ እግሮቿን ዘርግታ በምዕራብ እየሩሳሌም በሚገኘውና ዌስተርን ዎል በሚባለው ሥፍራ ፎቶ ከተነሳች በኋላ ነው። ይህ ሥፍራ ለአይሁድ እምነት ተከታዮች እጅግ የተቀደሰው ቦታ ነው።

የሃይማኖት አባቶች የሞዴሏን ድርጊት በጠንካራ ቃላት ካወገዙ በኋላ በጻፈችው የመልስ ማስታወሻ ተሳልቃባቸዋለች።

"ፈጣሪ ሰውነታችንን ፈጠረ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ይህን ማለታቸው ግራ አጋብቶኛል። እንዴት ነው ጡቶቻችንና መራቢያዎቻችንን የሚጨምረው ገላችን ራሱ ፈጥሮት በዚህ ደረጃ ሊወገዝ የሚችለው?" ብላለች።

አንዳንድ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች ሞዴሏ በኢስላም የተቀደሱ ሥፍራዎችን ትታ በአይሁዶች ቅዱሳን ስፍራዎች እርቃኗን ፎቶ መነሳቷ "እስራኤል ጠል" መሆኗን ያመለክታል ብለዋታል።

እርሷ ግን ትችቱን አጣጥለዋለች። በእርግጥም በሌላ አንድ የዕርቃን ፎቶዋ ላይ አልአቅሳ በርቀትም ቢሆን ይታያል።

ተያያዥ ርዕሶች