የአለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች

የቢሲው ስፖርት ተንታኝ ማርክ ላውረንሰን በምድብ ከተደረጉ 48 ጨዋታዎች መካከል 22ቱን በትክክል ገምቷል።16ቱን ከተቀላቀሉት ሃገራት መካከል የትኞቹ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ያመራሉ? ላውሮ ግምቱን አስቀምጧል።

ፈረንሳይ ከአርጀንቲና

አርጀንቲናዎች ተከላካይ መስመራቸው ጥሩ ነው ብዬ አላስብም። በተቻላቸው መጠን ነገሮችን ቀለል አድርገው መጫወትና በተረፈ ደግሞ የሊዮኔል ሜሲ ብቃት ላይ ተመስርተው መጫወት ነው የሚመርጡት።

አርጀንቲና በአጣብቂኝ ወደ ቀጣዩ ዙር ስታልፍ፤ ፈረንሳይ ግን በቀላሉ ነበር የምድብ ጨዋታዎቿን ያጠናቀቀችው።

ፈረንሳይ አሁንም ቢሆን ኦሊቪዬ ዡሩ ከፊት ሆኖ ከኋላው ፖል ፖግባና ንጎሎ ካንቴ ካሉ በጣም አስፈሪ ቡድን ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ሆነም ቀረም ፈረንሳይ 2-1 ታሸንፋለች ሲል ላውሮ ግምቱን አስቀምጧል።

ኡራጓይ ከፖርቹጋል

ይህ ጨዋታ ለመሃል ዳኛው አስቸጋሪ ይሆንበታል። የኡራጓይ ተከላካዮች ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለማስቆም የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ጨዋታውን በጣም ፈታኝ እንዲሆን ያደርገዋል የላውሮ አስተያየት ነው።

ፖርቹጋል አጨዋወቷን ትቀይራለች ብዬ ኣላስብም። ኡራጓይ ደግሞ አጥቂ መስመሯን እስካሁን አልተጠቀመችበትም ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ሲደርሱ አስፈሪዎች ናቸው።

ጨዋታው በኡራጓይ 1-0 አሸናፊነት ይጠናቀቃል።

ስፔን ከሩሲያ

ምንም እንኳን ሩሲያ በምድብ ጨዋታዎች ብታስገርመንም፤ የስፔን አጨዋወትን ግን ትቋቋመዋለች ብዬ አላስብም።

የሩሲያ ደጋፊዎች ያለምንም ጥርጥር ቡድናቸውን እስከመጨረሻው ቢያበረታቱም፤ ስፔን የጨዋታ የበላይነት ይኖራታል ብዬ አስባለሁ።

በጨዋታውም ስፔን 2-0 አሸንፋ የሩሲያ ደጋፊዎችን አንገት ታስደፋለች።

ክሮሺያ ከዴንማርክ

በዚህኛው የአለም ዋንጫ ክሮሺያዎች በጣም አስገርመውኛል። በሙሉ ጨዋታዎቻቸው ላይ የመሃል ክፍሉ እጅግ የተዋጣለት የነበረ ሲሆን፤ የፊት መስመራቸውም ቢሆን በደንብ የተደራጀ ነው።

በሌላ በኩል ዴንማርክ ግን አጨዋወታቸው የተለመደ ነበር። ጥቂት የጎል እድሎች እንደሚፈጥሩ አስባለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ ኣላስብም። ምናልባት ክርስቲያን ኤሪክሰን ሊጠቅማቸው ይችላል።

ጨዋታውን ግን ክሮሺያ 2-0 ታሸንፋለች።

ብራዚል ከሜክሲኮ

ብራዚል ከሜክሲኮ የምታድርገው ጨዋታ ቀላል ይሆንላታል ብዬ አላስብም። ከሜክሲኮ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን ያሸነፉ ሲሆን፤ ሜክሲኮ በበኩሏ ከብራዚል ካደረገቻቸው ከአስራ አምስት ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፋ ሶስቱን ብቻ አቻ ወጥታለች።

ስለዚህ ሜክሲኮ ብራዚልን መግጠም እንደ ሌሎች ቡድኖች ብዙም አያስፈራትም። ብራዚል ደግሞ ገና ቡድኑ እየተዋሃደ ይመስላል፤ ኔይማር ወደ ሙሉ አቋሙ ሲመለስ ግን እጅግ አስፈሪ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።

በጨዋታው ብራዚል 2-0 ታሸንፋለች ብዬ እገምታለሁ።

ቤልጂየም ከጃፓን

ጃፓን ካለችብት ምድብ ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋ ለእንግሊዝ እና ቤልጂየም ፈተና ትሆላለች ብዬ ገምቼ ነበር። ነገር ግን ከምድባቸው ማለፍ አልቻሉም።

ቤልጂየሞች ይሀ ጨዋታ ይከብዳቸውል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ብዙ የግብ እድሎችን ይፈጥራሉ።

ጨዋታውን ቤልጂየም በቀላሉ 2-0 ታሸንፋለች ብዬ አስባለሁ።

ስዊድን ከስዊዘርላንድ

ስዊዘርላንድ በምድብ ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጋለች። ከባድ ፈተናም አጋጥሟታል ብዬ አላስብም።

ሰዊድኖች ደግሞ አሪፍ የሚባል አጥቂ ባይኖራቸውም፤ እስከመጨረሻው የሚታገሉ ተጫዋቾች አሏት።

እስካሁን ያደረጉትን ጨዋታ ከግምት ውስጥ በማስገባት' ስዊዘርላንድ 1-0 ታሸንፋለች።

ኮሎምቢያ ከእንግሊዝ

እንግሊዝ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታዋ በቤልጂየም መሸነፏ ብዙ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም። ኮሎምቢያዎች ደግሞ ጥሩ የሚባሉ የፊት መስመር ተጫዋቾች አሏቸው፤ ነገር ግን ተጭነው የሚጫወቱ የእንግሊዝ ተጫዋቾችን ይቋቋማሉ ብዬ አላስብም።

በጨዋታው እንግሊዝ 2-0 ታሸንፋለች።