የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

የፎቶው ባለመብት, YONAS TADESSE

ወታደርም፣ አርሶ አደርም፣ ላብ አደርም ነበሩ። ብዕረኛ ስለመሆናቸው ግን የሚያውቅም ያለም አይመስልም…። ምናልባት ቴዎድሮስ ተሾመ?

እርሱ እንደሚለው ከቀዝቃዛ ወላፈን ውጪ ሁሉም ሥራዎቹ ላይ የዶክተር ዐብይ አሻራ አለ። ይህን አባባል ካፍታታነው ደራሲ ዐብይ ‹‹አባይ ወይስ ቬጋስ››፣ ‹‹ፍቅር ሲፈርድ››፣ ‹‹ቀይ ስህተት›› እና ሌሎች 8 የቴዎድሮስ ፊልሞች ላይ በኅቡዕ አንዳች የሐሳብ መዋጮ ሳያደርጉ አልቀሩም።

ይህ ነገር የሰውየውን መግነን ተከትሎ ራስን ከዚያው ተርታ ለማሰልፍ የተቀነባበረ የዝና ሻሞ ይሆን ወይስ ሰውየው የምርም ጸሐፊ ናቸው?

ከሆኑስ የኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር የፈጠራ ድርሻ እንዴት ይመተራል? በ‹‹ሦስት ማዕዘን›› ውስጥ እርሳቸው ስንት ማዕዘናትን አሰመሩ?

ይህን ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ከሴባስታፖል ሲኒማ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ጋር አወጋን፡፡

ፊልም የሚጽፍ ጠቅላይ ሚኒስትር?

ፊልም የሚመርቅ ሚኒስትር አጋጥሞን ሊሆን ይችላል። ፊልም የሚጽፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን…? እንጃ! ሐሳቡ ራሱ ወለፈንድ ይመስላል።

ዐብይ አሕመድ በቅድመ ንግሥና ወይም ከ4 ኪሎ ደጅ ፊልም ለመጻፍ የመጀመርያው መሪ ሊሆኑ ይችሉ ይሆን እንጂ በብዕር ሥም መጽሐፍ ለማሳተም ብቸኛው ጠቅላይ አይደሉም።

የቀድሞው የመለስ ዜናዊ ‹‹ምኩሕኳሕ ዘይፍለዮ ማዕፆ›› የሚል ልቦለድ መጽሐፍ ተስፋዬ የኋላሸት በሚባል የብዕር ሥም መጻፋቸው ይነገራል። ‹‹ማንኳኳት ያልተለየው በር›› እንደማለት ነው ርዕሱ በአማርኛ ሲመነዘር። ‹‹ገነቲና›› የሚል ሌላ መጽሐፍ እንዳላቸውም በገደምዳሜ ይወራል።

ዐብይ አሕመድ ደግሞ ‹‹ዲራዐዝ›› በሚል የብዕር ስም ‹‹እርካብና መንበር›› እንዲሁም ‹‹ሰተቴ›› የተሰኙ መጻሕፍን አበርክተዋል እየተባለ መወራት ከጀመረ ሰነባበተ።

‹‹ዲራዐዝ›› ቢያንስ የርሳቸውና የባለቤታቸው ምህጻር መያዙን መጠርጠር ይቻላል። ቀሪ ሆሄያት የልጆቻቸው ስሞችን የሚወክሉ ይሆኑ? ቴዎድሮስ በዚህ ጉዳይ ምንም ማለት አይፈልግም። ትውውቃቸው ከጅማ ይሁን ከአጋሮ፣ ከተማሪ ቤት ይሁን ከጉልምስና ፍንጭ ሰጥቶም አያውቅም። ከቢቢሲ ለቀረበለት ተመሳሳይ ጥያቄም ‹‹ይለፈኝ›› ሲል መልሷል።

ባይሆን ሁለቱ የጥበብ ሥራዎቻቸውን ከድሮም ጀምሮ እንደሚገማገሙ ይናገራል። ‹‹በሥራዎቼ ውስጥ ዐብይ አለ፣ በዐብይ ሥራዎቹ ውስጥ እኔ አለሁ።››

በደራሲ ዐብይ መጻሕፍት ጀርባ የቴዎድሮስ የሽፋን አስተያየት (blurb) መጻፉም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

የዐብይ አሕመድ ‹‹ሰተቴ›› ሌላው መጽሐፍ ነው። ጅማ ውስጥ የነበረ ‹‹ከድር ሰተቴ›› የሚባል ሰው ታሪክ ነው።

የመናገር ነጻነት ባልነበረበት በደርግ ወቅት በጅማ አደባባይ መንግሥትን ልክ ልኩን የሚናገር ነበር አሉ። በዚህ የተነሳ ደርጎች በየጊዜው የሚቀፈድዱት ሰው እንደነበረና በመጨረሻም ከሰዋራ ቦታ እንደገደሉት ቴዎድሮስ ‹‹የደራ ጨዋታ›› ለተሰኘው የራዲዮ ፕሮግራም ተናግሮ ነበር።

ዶክተር ዐብይ ታዲያ በዚህ አማጺ (Rebel) ስም ለምን መጽሐፍ መጻፍ ፈለጉ? ለምንስ ዲርዐዝ በሚል የብዕር ስም አሳተሙት? ብለን ብንጠይቅ ከመልስ ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄን እንቆሰቁሳለን።

‹‹ከድር ሰተቴ የነጻነት ታጋይ ስለነበረ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ለዚሁ ይመስለኛል›› ይላል ቴዎድሮስ፡፡

ምን ማለቱ ይሆን?. . .

ዶክተር ዐብይ የደበቁን መጽሐፍ አለ?

ለቴዎድሮስ ተሾመ ዐብይ አሕመድ የቀንተሌት ትጉህ አንባቢ ብቻ አይደሉም። ለመሪነት የተቀቡ ደግ ሰው ብቻም አይደሉም። ብዙ ነገሩ ናቸው።

ከሁሉም በላይ ግን ‹‹ነፍሱ ለጥበብ የቀረበች ናት›› ይላል። ለዚህም ነው ‹‹ከርሱ ጋር አንድ ሰዓት መቀመጥ አንድ ዓመት ትምህርት ቤት የመግባት ያህል የሚሆነው›› ሲል ምስክርነቱን የሚሰጠው።

ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን አሳይተውት ከሆነ ከቢቢሲ የተጠየቀው ቴዎድሮስ ‹‹አያዎ›› ምላሽ ከሰጠ በኋላ ሕዝብ የማያውቃቸው ሥራዎች እንዳሏቸው ግን አልሸሸገም።

ምናልባት የግጥም መድብሎች፣ ምናልባት የቴአትር ቃለ ተውኔቶች፣ ምናልባት አጫጭር ልቦለዶች? ምናልባት የፊልም ስክሪፕት? ቴዎድሮስ ለዚህ ምንም ፍንጭ አልተውልንም።

በ‹‹ሦስት ማዕዘን›› ግን የዶክተሩ ድርሻ 50 እጅ እንደሚይዝ ይናገራል። ርዕሱ እና የመጀመርያው ረቂቅ የርሱ እንደሆነ ካተተ በኋላ ‹‹ስሱ (sensitive) የሆኑና ፊልሙ ላይ የሚገኙ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እሱ ነው ያስተካከላቸው›› ይላል።

‹‹ብዙ ሰው የሱን ሥራ በስሜ ያወጣሁ አድርጎ ይተቸኛል፡፡ የሱን ስም ያልጠቀስኩት መጠቀስ ስለማይፈልግ ነው፤ ሆኖም ግን እኔና እሱ በምንግባባበት መንገድ አመስግኜዋለሁ›› ይላል ቴዎድሮስ።

ለካንስ ፊልሙ ሲጠናቀቅ ከሚመሰገኑ ሰዎች ዝርዝር ‹‹ዐብይ ወንድሜ›› የሚለው ውክልና ለአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, ASHRAF SHAZLY

የሦስት ማዕዘን ክብነት

በፍቅራቸው ተነድፈናል የሚሉ ዜጎች በበረከቱበት፣ የተናገሯቸው ቃላት እንደ ቆሎ በሚቆረጠሙበት፣ ከአፋቸው ማር ጠብ ይላል በሚባልበት፣ በዚህ የሰበር ዜና ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገደምዳሜም ቢሆን ‹‹ፊልም ጽፌ ነበር›› ሲሉ ሕዝቡ እንደ ዋዛ ያልፈዋል ተብሎ አይጠበቅም። የሆነውም ይኸው ነው።

‹‹ሦስት ማዕዘን›› ከሲኒማ ከወረደ ዘመን የለውም። አሁን ግን ፊልሙን ወደ ሲኒማ ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለምን ከተባለ ‹‹ብዙ ሰዎች ያን እንዳደርግ እየጠየቁኝ ነው። እኛም እየተዘጋጀን ነው›› ይላል ቴዎድሮስ።

እስከዚያስ? መታገስ ያልቻሉት በይነመረብ ላይ ተኮልኩለዋል። የተመልካቾ ቁጥር ባለፉት ሳምንታት ብቻ በእጥፍ ጨመሮ ታይቷል።

ይህ ሒሳዊ ሐተታ እስሚዘጋጅበት ዕለት ድረስም ለግማሽ ሚሊዮን የተጠጉ የበይነ መረብ ታዳሚያን ፊልሙን ደጋግመው አጫውተውታል። ከነዚህ ወስጥ ገሚሶቹ በፊልሙ ላይ የዶክተር ዐብይን ተሳትፎ በመስማታቸው ብቻ ፊልሙን ለመኮምኮም ዳግም የመጡ ናቸው። ይህንኑ አስያየታቸውን እዚያው ከፊልሙ ሥር በተሰጣ የበይነመረብ አስተያየት መስጫ ሰሌን ገልጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ፊልሙ እንዲታይላቸው መፈለጋቸውን አልሸሸጉም። ‹‹…ሦስት ማዕዘንን ያላያችሁ ሰዎች በደንብ እንድታዩት በዚህ አጋጣሚ እመክራችኋለው›› ነበር ያሉት፣ በዚያች ምሽት የእራት ግብዣ።

‹‹…አትናገር ብዬው እኔው ራሴ አፈረጥኩት››

ዶክተር ዐብይ ድርሰቱን ስለመጻፋቸው ይፋ ያደረጉበት አጋጣሚ የሰውየውን ቀደምት ትልም እንድንመረምር ይጋብዛል።

የአስመራን ልዑክ እራት በጋበዙበት ምሽት የአገራቱን ወንድማማችነት እያጎሉ በመናገር ላይ ነበሩ። ሊያውም በተፍታታ ስሜት። በእያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር ማሳረጊያ ጭብጨባ ያጅባቸው እንደነበር ልብ ይሏል።

‹‹…እነ ጥሩዬ በአስመራና በምጽዋ ለመሮጥ በጣም ጓጉተዋል።›› ካሉ በኋላ የኛ በርካታ አርቲስቶች በፊልም በሙዚቃ የሁለቱን አገራት ወንድማማችነት ለማሳየት ጥረት ማድረጋቸውን ጠቀሱ። ቀጥለው ይህን ያደረጉ አርቲስቶችን በስም ይጠቅሳሉ ብለን ስንጠብቅ ራሳቸውን አስቀድመው አስገረሙን።

‹‹እኔም በተወሰነ ደረጃ በደራሲነት የተሳተፍኩበት ሦስት ማዕዘን የሚያስተላልፈው አንዱ መልዕክት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ወዳጅነት በችግር ጊዜ ምን እንደሚመስል ነው።››

ለዓመታት በምስጢር የያዙትን ጉዳይ ይፋ በማድረግና ባለማድረግ ቀልባቸው መወላወሉን በሚያሳብቅ ድምጽ እንዲህ አሉ፣ ‹‹ለረዥም ጊዜ ቴዲን አትናገር ብዬው ዛሬ እኔው ራሴ አፈረጥኩት።››

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቀዝቃዛ ትንቢት

ሦስት ማዕዘን ከተደረሰ ሰባት ዓመታት አልፎታል። ያኔ የፊልሙ ገሚስ-ደራሲ ዐብይ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ። ያኔ 'ዐብይ' የሚለው ቃል ተውላጠ ስም እንጂ የ 'ንጉሥ' ስም መሆን አልጀመረም ነበር።

ቴዎድሮስ እንደሚያስታውሰው ከሆነ ሰውየው መሪ እንደሚሆኑ ገና ድሮ ያውቁ ነበር ‹‹ (ለመሪነት) እየተዘጋጀ እንደነበር አውቃለሁ።››

ያኔ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉትም ምናልባት ለዚሁ ይሆን? ለነገሩ ፎቶ መነሳት የማይወዱትም ለዚሁ እንደነበር ተናግረው ያውቃሉ። ሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ሳሉ አንዲት ፈረንሳዊት አፍቅራቸው ይዤህ ልጥፋ ስትላቸው እንዴት ብትንቀኝ ነው ብለው ማልቀሳቸውን ልብ ይሏል።

‹‹አንተስ ጓደኛህ ዐብይ አንድ ቀን መሪ እንደሚሆን ሽው ብሎህ ያውቃል?›› በሚል ከቢቢሲ የተጠየቀው ቴዎድሮስ ‹‹የማላውቅ መቼ የሚለውን ብቻ ነበር›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የደራሲ ዐብይ የንግርት ቴክኒክ (Foreshadow)

ንግርት በፈጠራ ሥራዎች በተለይም በተንቀሳቃሽ ምስልና በልቦለድ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኝ የጎበዝ ደራሲዎች መለያ ቴክኒክ ነው። ሁሉም እግር ኳስ ተጫዋቾች ጎል ያስቆጥሩ ይሆናል። እንደ ሮናልዲኒሆ ጎቾ ግን በኳስ ቅኔ አይቀኙም። ሁሉም ደራሲ ሊሞነጫጭር ይችላል። ንግርትን የሚችሉት ግን ጥቂቶች ናቸው።

በፊልሙ ውስጥ ወይም ከዚያም ባሻገር ባለ የእውን ዓለም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር በስሱ ጠቆም አድርጎ የሚያልፍ ጥበባዊ ትንቢት ነው-ንግርት። ደራሲዎች እንደ ባሕታዊ ሲሰራራቸው ታይቶኝ ነበር የሚሉባት አትሮንስ ናት-ንግርት።

ደራሲ ዐብይ ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመተንበይ እንዲያ ያለ ቴክኒክ ሳይሞካክሩ የቀሩ አይመስልም። የሞከሩበት መንገድ ግን ግልብ ነው፤ አልሰወሩትም። አጻጻፋቸውም ቢሆን ደርዘኛና አማላይ ኾኖ አይታይም። ይህ ጨለም ያለ ድምዳሜ በሦስት ነገረ ማገሮች (Core Points) ሊፍታታ ይችላል።

አንደኛው ቴዎድሮስ ተሾም ረቂቁን ሲያሳያቸው አፍርሰው መሥራታቸው ነው። እርሱ እንደሚለው የመጀመርያው ረቂቅ እንደተለመደው እኩይና ሰናይ ገፀ ባሕርያት ሰዋዊ ሆነው የቀረቡበት ነበር። ወይም ደግሞ ኤርትራና ኢትዮጵያዊያን በፊልሙ ውስጥ አንዱን ሰናይ ጀግና ሌላው እኩይ ባላንጣ (hero and villain) ሆነው ነበር የተሰለፉት።

ዶክተር ዐብይ ‹‹የለም ይሄ መሆን አይገባውም›› አለ። ሁለቱን አገሮችማ እርስበርስ ጠላት አናድርጋቸው። ‹‹ባይሆን በጋራ በሚደርስባቸው ችግር ሲፈተኑ ነው ማሳየት ያለብን ብሎ ስክሪፕቱን እንደገና ጻፈው›› ይላል ቴዎድሮስ።

በፊልሙ ውስጥ ታዲያ ጥበባዊ ውበት በራቀው መንገድም ቢሆን ሁለቱ አገሮች መቼም ወንድማማች እንደሆኑ፣ ብሎም ዐሐዳዊነት እጣ ፈንታቸው እንደሚሆን ለማሳየት ደራሲ ዐብይ ብዙ ለፍተዋል።

በፊልሙ እንደ ኤርትራዊት ፍልሰተኛ ሆና የምትተውነው ማኅደር አሰፋ በጉዞ ላይ ችግር ሲያጋጥማት የሚደርሱላት ኢትዮጵያዊያን ሆነው ተስለዋል። በተለይም በፍቅሯ የተነደፈው ሌላው ፍልሰተኛ ሰለሞን ቦጋለ ኢትዮጵያን ወካይ ገጸ ባሕሪ ኾኖ ተጫውቷል።

ኤርትራዊቷ ማኅደር አሰፋ ጨርቆስ አካባቢ የተወለደች ስትሆን ነጻነት ተከትሎ ኤርትራ የአፍሪካ ሲንጋፖር ልትሆን ነው በሚል ተስፋ ቤተሰቦቿ ወደ አስመራ ይዘዋት እንደሄዱ በፊልሙ ትተርካለች፡፡ ያ ተስፋ ከንቱ ሲሆን ስደትን ትመርጣለች፡፡

ማኅደር በፊልሙ ላይ ስትሳል አማርኛ የማትችል መስላ ብትቆይም የኋላ ኋላ ቅኔ መቀኘት የሚያስችል አማርኛን ስታቀላጥፈው እንመለከታለን፡፡ ደራሲ ዐብይ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው? ይዘገይ ይሆናል እንጂ መደመራችን አይቀርም ማለቱ ይሆን? ላይ ላዩን እያስመሰልን ነው እንጂ ውስጣችን አንድ ነው ማለቱ ይሆን? ሁለት ቋንቋ በመናገር የተቀናነስን እንመስላለን እንጂ ለመደማመር የተፈጠርን ሕዝቦች ነን ለማለት ይሆን?

ማኅደር አሰፋ በሊቢያና በሜክሲኮ በረሃ ስትወድቅ የደረሰላት ኢትዮጵያን እንዲወክል የተደረገው ሰለሞን ቦጋለ ነው።

ለምሳሌ ሜክሲኮ በሞት አፋፍ ላይ ለነበረችው ማኅደር ደም ለጋሽ ጠፍቶ ጀማል የሚባለው ገጸ ባሕሪ ደም በመስጠት ሕይወቷን ይታደጋታል። ማኅደር አሰፋ ከሰመመን ስትነቃም ‹‹ለማላውቃት ለኤርትራዊ ደም ሰጠሁ›› ይላል፤ ኢትዮጵያዊው ጀማል። ጀማል የጅማ ልጅ ሳይሆን አይቀርም። ቴዎድሮስም የጅማ ልጅ ነው። ዶክተር ዐብይም ከዚያው አካባቢ ነው። ሦስት ማዕዘን።

ከዚህም ሌላ ንግርት የሚመስሉ በግልብ ቋንቋም ቢኾን በዐብይ አሕመድ በተሳሉ ገጸ ባሕርያት የሚነገሩ ‹‹የአንድ ነን›› ትርክቶች በፊልሙ ላይ እዚህም እዚያም ይገኛሉ።

ማኅደርን የሊቢያ ንዳድ አዝለፍልፎ ሲጥላት ሰለሞን ቦጋለ (ኢትዮጵያ) ከተቀረው ስደተኛ (ከአካባቢው አገራት) ሁሉ ተለይቶ ማኅደርን ጥዬ አልሄድም ይላል። ጓደኞቹ ‹‹እርሷ እኮ ኤርትራዊት ናት›› ቢሉትም ‹‹ለኔ ያ ልዩነት የለውም›› ሲል ይሟገታል። በአረብ የባሪያ አስተላላፊዎች ልትደፈር ስትል የሚደርስላትም ይኸው ኢትዮጵያዊ ነው። ነገሩ የአካባቢውን ጂኦፖለቲክስ በፊልም ጥበብ ለመነካካት ይመስላል።

ይልቅ አጨራረሱን ችለውበታል።

ሜክሲኮ ድንበር ላይ ማኅደር አሰፋ (ኤርትራዊት) እና ሰለሞን ቦጋለ (ኢትዮጵያዊ) ቃል ኪዳን ያስራሉ። ቃል ኪዳን ያሰሩበት መንገድ ለጥጠን ከተረጎምነው ‹‹አሰብ›› የሚል ፖለቲካዊና ፍካሪያዊ ትርጉም ሊሰጠን ይችላል።

ማኅደር አሰፋ፡- ‹‹ነፍሴን አትርፈክልኛል ከዚህ በኋላ ነፍሴ የኔ አይደለችም፤ ያንተ ናት›› ካለች በኋላ ከዞማ ጸጉሯ ጫፉን ሳትሰስት ቆርጣ በሰለሞን ቦጋለ ጣት ከጸጉሯ የተገመደ የጋብቻ ቀለበት ሠርታ ታጠልቅለታለች።

ደራሲ ዐብይ አሕመድ በዚህ ንግርት ምን ሊተነብዩ እየሞከሩ ይሆን?

ዶ/ር ዐብይ ጎበዝ ጸሐፊ ናቸው?

ፊልምን ፊልም የሚያደርገው የፊልም ጽሑፉ ብቻ ቢሆን ኖሮ መራር ሐያሲያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹ለዛሬ አልተሳካሎትም›› ባሏቸው። ለምን?

ደራሲው እንዲሆኑ የሚመኝዋቸውን ሕልሞች ሁሉ ሳይመሰጥሩ እንዲሁ እንደነገሩ ያዘንቧቸዋል። እርግጥ ነው ፖለቲካዊ ምኞታቸው የሚያማልል ነው። ኾኖም ምኞቱ የተጻፈው በኑዛዜ ቋንቋ ነው። በጥበብ ቅመም አልታሸም። በውብ ቋንቋ አልተዋዛም። ጥፍጥ፣ ክሽን፣ ምጥን አልተደረገም።

ፊልሙ ብዙ የሚወደሱለት ሙከራዎች ቢኖሩትም ብዙ ፊልሞቻችንን የሚያስነጥሱ ጉንፋኖች እሱም ላይ በርትተው ይታያሉ። ምናልባት በፊልሙ መጨረሻ የምንማረው ስደት ብቻ ሳይሆን ፊልም መሥራትም አስቸጋሪ መሆኑን ነው።

ሁሉንም ኩነት በተራዘመ ቃለ ተውኔት ለተደራሲ ለማተት ይሞክራል። ከድርጊት ድርጊት ቶሎ ስለማይሸጋገር አንድ ታዳሚ ፊልሙን አቋርጦ ውልና ማስረጃ ጉዳይ ጨርሶ ቢመለስና ፊልሙን ማየት ቢቀጥል እምብዛምም የሚያጣው ነገር የለም። እርግጥ ነው ይህ ገለጻ ተጋኖ ሊሆን ይችላል። ውልና ማስረጃ ፈጣን አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት መሆኑንም መዘንጋትም አያሻም።

ፊልሙ ላይ የሚተውኑ ሌሎች ፀጉረ ልውጥ የሜክሲኮና የአረብ ዝርያ ያላቸው ተዋንያን ለምን በተሻለ እንደተወኑ ሆኖ እንደሚሰማን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ምናልባት እነ ሰለሞን ቦጋለን፣ እነ ማኅደር አሰፋን፣ እነ ሳምሶን ታደሰ ቤቢን፣ እነ ሰላም ተስፋዬን እጅግ ተላምደናቸው ይሆን? ለዚያ ይሆን በየበረሃው እንግልታቸውን እያየን ነገር ግን የማናምነው? በሌላ አነጋገር ፊልም እየሠሩ እንደሆነ ሳናስብ ፊልሙን አንጨርሰውም።

አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ሐያሲ ‹‹ፊልሙን ከመጨረስ በረሀውን ማቋረጥ ሳይቀል አይቀርም›› ያለው ነገር ርሕራሄ ያጣ ሂስ ሊባል ይችላል እንጂ እውነትነት የለውም የሚባል አይደለም።

ያም ሆኖ ፊልሙ በርከት ባሉ አገራት እየተንሸራሸረ አክሊል ደፍቷል።

በደቡብ አፍሪካ ‹‹አፍሪካን ሙቪ አካዳሚ አዋርድ››፣ ለዚያውም በሦስት ዘርፍ አሸንፏል። በፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል እንዲሁ ሌላ ዋንጫ ወስዷል። በሩዋንዳ ‹‹ቤስት ኦዲየንስ ፊልም አዋርድም›› እንዲሁ።

ፊልሙ በተጫነበት የዩቲዩብ መስኮት ሥር የተሰጡ አያሌ አስተያየቶች ይህን ሲኒማ እያነቡ ጭምር እንደተመለከቱት የሚናዘዙ ናቸው። ስለዚህ እንደ ስውሩ ደራሲ ዶክተር ዐብይ ሁሉ ፊልሙም ሰፊ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ እንደሆነ ሊካድ አይገባም።

ቴዎድሮስ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ፊልሙ በሐያሲያን ዘንድ ደካማ እንደሚባልና ለድክመቱ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ይወስዱ እንደሁ ሲጠይቅ ‹‹ያ የዳይሬክተሩ እንጂ የደራሲው ችግር አይደለም›› ሲል ተከራክሯል።

‹‹ፊልም እኮ የድርሰት ውጤት አይደለም፡፡ እንዲያውም ለፊልም ውድቀትም ሆነ ስኬት ተጠያቂ መሆን ያለበት ዳይሬክተሩ ነው፡፡ ስለዚህ ችግር አለ ከተባለም የእኔ የዳይሬክተሩ ነው እንጂ የሚሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አይደለም።››