ኬንያዊው በኮንዶም ምክንያት መንግሥትን ከሰሰ

የተለያዩ የኮንዶም ዓይነቶች Image copyright MANAN VATSYAYANA

አንድ ኬንያዊ ግለሰብ "ኮንዶም ተጥቅሜ ግብረ-ስጋ ብፈፅምም ለአባላዘር በሽታ ተጋልጫለሁ" በማለት መንግሥትን ከሷል።

ግለሰቡ የከሰሰው የመንግሥት ጥራት ተቆጣጣሪ፣ የገቢዎች መሥሪያ ቤትንና ቤታ የተሰኘ መድሃኒት አስመጪ ድርጅትን ነው።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልተፈለገው ይህ ግለሰብ "ሶስቱ መሥሪያ ቤቶች ተጠቃሚዎችን ከመሰል ክስተቶች መጠበቅ አልቻሉም" ሲል ወንጅሏል።

መሥሪያ ቤቶቹ ስለክሱ ያሉት ነገር እስካሁን መገናኛ ብዙሃን ጆሮ አልደረሰም።

ግለሰቡ በሽታው ወደባለቤቱ መተላለፉን በመግለፅ ሁኔታው 'ከባድ' መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሯል።

"ኮንዶሞቹን የገዛሁት የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ነው" ያለው ከሳሽ ትንሽ ቆይቶ ህመም ይሰማው እንደጀመር አሳውቋል።

"ሁኔታው እጅግ ቢጨንቀኝ ጊዜ ነው ወደ ባህል ሃኪም የሄድኩት" ያለው ከሳሽ ኮንዶሙ ለህመሙ ምክንያት መሆኑን ለመረዳት ብዙ እንዳልፈጀበት አሳውቋል።

"ክስተቱ ጎድቶኛል፤ ተቃውሻለሁ፤ መጠጥ ማዘውተርም የጀመርኩት ከዚያ በኋላ ነው" ሲል ከሳሽ ክሱን አሰምቷል።

በዚህ ምክንያት ሥራውንና ቤተሰቡን እንዳጣ የተናገረው ግለሰብ የፍርድ ያለህ እያለ ይገኛል።

ተያያዥ ርዕሶች