"መንግሥት የሚደግፈው የሙስሊሙን ሕብረተሠብ ነው" ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሀመድ ከየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን እና ከቅርብ ወራት በፊት ከእስር የተፈቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር ተወያይተዋል Image copyright ETV

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የሚወክል ትልቁ የአስተዳደር እርከን ተደርጎ ይታሰባል። ሆኖም ይህ መጅሊስ ለዓመታት የፖለቲካ ገለልተኛንትና የውክል ጥያቄ ሲነሳበት ነው የኖረው።

ይህንንና በርካታ ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሕዝበ ሙስሊሙ ተቋቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከዓመታት በፊት ከመንግሥት ጋር ንግግር ጀምሮ የነበረ ሲሆን ወደ ኋላ ላይ ግን በሽብር ክስ አባላቱ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን እና ከቅርብ ወራት በፊት ከእስር የተፈቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው አወያይተዋል።

ዶክተር ዐብይ በሁለት ፈረቃ ነበር ሁለቱን አካላት ያነጋገሩት።

"በውይይቱ ወቅት ይዛችሁ የገባችኋቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምን ነበሩ?" በማለት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባልና የኮሚቴው ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ አህመዲን ጀበልን ቢቢሲ ጠይቋቸው ነበር።

እሳቸውም ሲመልሱ፣" መጅሊስ የሕዝበ ሙስሊሙ ተቋም ቢሆንም፤ በተግባር ደረጃ ግን ላለፉት ዓመታት የማኅበረሰቡ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መዝለቁን" ካብራሩ በኋላ "ይህም የሆነው ተቋሙ ህዝቡ እንደሚፈልገውና ሕጉ እንደሚፈቅደው ምርጫ አለማካሄዱ፤ የመንግስት ጣልቃ ገብነት መኖሩ ነበር" ብለዋል።

በተለይም ከዐብይ አሕመድ በፊት የነበረው የመንግሥት አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያትና በተደጋጋሚ የደህንነት አካላቱ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ሁሉን አቀፍ ጣልቃ ገብነት ተለይቷቸው እንደማያውቅ አቶ አሕመዲን ያስረዳሉ።

የፌዴራል ጉዳዮችም ተመሳሳይ ችግር ይፈጥር እንደነበር አስታውሰዋል።

የዛሬ 10 ዓመት በዶክተር ጀይላን ከድርና ሙፍቲህ ሀጅ ዑመር ኢድሪስ መሪነት ልዩነቶችን ለመቅረፍ ውይይት ተደርጎ በደኅንነት ሰዎች እንዲመክን መደረጉንም አውስተዋል።

ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ያኔ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮችና የኢትዮጵያ ኡለማ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ተናግረው "በነአባይ ጸሐዬና በደህንነቶች ተገምግመው ነው በወቅቱ አርፈህ ተቀመጥ የተባሉት" ይላሉ አቶ አሕመዲን፣ በወቅቱ የደህንነቱ ጣልቃ ገብነት እስከምን ደረጃ ድረስ እንደነበር ሲያስረዱ።

አዲሱ መጅሊስ እንዴት ይዋቀር?

በትናንቱ ውይይት በርካታ ጉዳዮች ቢነሱም በዋናነት ግን የውይይቱ ትኩረት የነበረው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመጅሊሱ ጉዳይ ነበር ብለዋል።

እንደ አቶ አሕመዲን ገለጻ በመጅሊሱ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ያስፈለገው አንድ ጊዜ ጠንካራ መጅሊስ ከተቋቋመ ሌሎች የሙስሊሙ ጥያቄዎች በዚያው እንደሚመለሱ ታሳቢ በመደረጉ ነው።

"ሁሉንም የሚያስማማ መጅሊስ ካለ፤ መንግስትም ለራሱ ሲል ይመልሰዋል፤ የሙስሊሙንም ጥያቄ እናንተ ትመልሱታላችሁ ወደሚለው ሃሳብ ስለተደረሰ ትኩረታችንን ወደ መጅሊሱ አድርገን ነበር" ይላሉ አቶ አሕመዲን።

በውይይቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አንድ ቀን ቀደም ብለው ከመጅሊሱ አመራሮች ጋር ውይይት እንዳደረጉና ችግሩ በተግባር እንዳለ ጠቅሰው ነበር።

በውይይቱ ወቅት አንዳንድ የመጅሊሱ አባላት መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴውን ለማጥላላት ሙከራ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

"የፖለቲካ ዓላማ አላቸው፤ አክራሪዎች ናቸው ሲሉ" ከሰውን ነበር ያሉት አቶ አሕመዲን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን "አሁን እንዲህ ዓይነት ወሬ የምናወራበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ የመወቃቀስ አዝማሚያውን ተችተዋል።

"እናንተ ላይ ጥያቄ የሚያነሳ የህብረተሰብ ክፍል አለ፤ ስለዚህ ኮሚቴው ሌላ አላማ አለው ብላችሁ መነሳት አትችሉም። ሌላ አላማ ቢኖራቸውም፤ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ተደራጅተው መጠየቅ መብታቸው ነው" በማለት ጠንካራ ወቀሳ በመጅሊሱ አመራሮች ላይ መሰንዘራቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር ዐብይ በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ገለልተኝነት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውንም ከአቶ አሕመዲን ጀበል ሰምተናል።

"መንግስት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ላይ ያላችሁትን መሪዎች አይደግፍም፤ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴውንም አይደግፍም፤ መንግሥት የሚደግፈው የሙስሊሙን ህብረተሰብ ነው" ማለታቸውን አቶ አሕመዲን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚመጥን ተቋም መፈጠር አለበት" ማለታቸውን አቶ አህመዲን ጨምረው ነግረውናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቀደም ብሎ መጅሊሱን ሲደግፉ የነበሩ የመንግስት አካላትን ክፉኛ ከወቀሱ በኋላ "መንግሥት እንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ እጁን አስገብቶ አንዱን የሃይማኖት ተቋም ደግፎ ሌላውን ነቅፎ መቆየቱ ስህተት ነበር" ብለዋል።

"እኔ እስካለሁ ድረስ እንዲህ ዓይነት ነገሮች አይኖሩም" ሲሉም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ማጠናቀቂያ "አሁን ያሉት የመጅሊሱ አባላት በህጋዊ መንገድ ሳይሆን በመንግስት ፈቃድ ነው የተመረጡት፤ ስለዚህ የሽግግር መጅሊስ ይቋቋም" ብለን ሃሳብ አቅርበን ነበር ያሉት አቶ አህመዲን፤ ሃሳባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳልወደዱትና ከዚያ ይልቅ ለሁሉም ችግሮች የመፍትሄ ሐሳብ የሚያቀርብ አዲስ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

የዚህ ኮሚቴ ዋና ሥራ ምንድነው በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

"አዲሱ ኮሚቴ የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች እንዴት ቢዋቀር የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ችግር መፍታት ይችላል? ሁሉም ሰው የሚወደውና የሚፈልገው ዓይነት መጅሊስ እንዴት ማቋቋም ይቻላል? የመጅሊስ ምርጫ የትና እንዴት ይደረግ? የሚሉትን ትያቄዎች አጥንቶ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ነው የተቋቋመው።"

አዲሱ ኮሚቴ በአገር ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪም ቢሆን በመንቀሳቀስ የሌሎች አገሮችን የመጅሊስ አወቃቀር ልምድ በማየት ያለቀለት ነገር ይዞ ማቅረብ ነው ስራው የሚሆነው ሲሉም አክለዋል።

አቶ አሕመዲን ጀበል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቀደም ብሎ የተቋቋመው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አዲስ በሚመሠረተው መጅሊስ ምንም ዓይነት የሥልጣን ፍላጎት የለውም።