ጠ/ሚ ዐብይ አልበሽርን የድንበር ግጭቱን አብረን እንፍታ አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር Image copyright Getty Images

በመተማ አካባቢ የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለኦማር አልበሽር መልዕክት እንደላኩ የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከሱዳኑ ፕሬዚዳንትና ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልዳርዲሪ መሀመድ ጋር በነበረ ውይይት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መልዕክቱን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር በድንበር ላይ የተከሰተውን ግጭትም ሁለቱም ኃገራት በጋራ መፍታት አለብን የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀጠናው ስላለው የፀጥታ ጉዳዮችም እንደተወያዩ ተዘግቧል።

ከሰባት መቶ ኪሎሜትር በላይ ርዝመት ያለውና በቅጡ ያልተሰመረውን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር ታክከው የሚኖሩ የምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አርሶ አደሮች ለውጥረት ባይታዋር ያለመሆናቸውን ይገልፃሉ።

ከትናንት በስቲያ ማለዳ ድንበር ተሻግረው በዘለቁ የሱዳን ወታደሮች ተፈፅሟል የሚሉት ጥቃት የውጥረቱ መገንፈል መገለጫ ነውም ይላሉ።

የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በድንበሩ አቅራቢያ ለሚፈጠሩ ግጭቶች እርሿቸው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ መሆኑ ሲዘገብ የቆየ ሲሆን ፤ አሁንም የጥቃቱ መንስዔ ከዚሁ እንደማይዘል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም ለክልሉ የብዙኃን መገናኛ በሰጡት ቃል ገልፀዋል።

ጥቃቱ ተፈፅሞበታል በተባለው ደለሎ አራት አካባቢ ማሣ እንደነበራቸው የነገሩን የአካባቢው ኗሪ፤ ቦታውን ሱዳን ይገባኛል እንደምትል ያስረዳሉ።

"አሁን ቁጥር አራት የሚጣሉበት የኢትዮጵያ መሬት ነው። የእኔ የእርሻ መሬት ነበር" የሚሉት ነዋሪው ታፍነው የተወሰዱ እንዲሁም አራት ሰዎች እንደሞቱም እንደሰሙም ተናግረዋል።

ሰባት ሰዎች እንደቆሰሉ የሚገልፁት እኚሁ የአይን እማኝ ሁለቱ የመከላከያ ኃይል አባላት ናቸው ብለዋል።

የክልሉ ዋና አፈ ቀላጤ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከብሄራዊው የቴሌቭዥን ጣብያ ጋር ባደረጉት ውይይት የሱዳንን ታጣቂዎች የሰርክ የእርሻ ስራቸውን በሚያከናውኑ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን አረጋግጠው ፤ታጣቂዎቹ "መሬቱ የእኛ ነው" የሚል ተገቢ ያለሆነ ጥቃት አንስተዋል ብለዋል።

አቶ ንጉሡ በግጭቱ ህይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያዊን ሁለት መሆናቸውን አክለው ተናግረዋል።

ከመተማ አርባ ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ግንደ ውሃ ከተማ ቁስለኞችን ህክምና እንዲያገኙ በማስተባበር ላይ መጠመዱን የገለፀልን ሌላ የአካባቢው ኗሪ በዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ ለማድረግ ወደስፍራው ማቅናት መጀመራቸውን ይናገራል፤

ከዚህም ተጨማሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ስፍራው ማቅናቱን ሰምቻለሁ ይላል። "ግጭቱ ተባብሶ ነው ያለው። ትናንትና የኃገር መከላከያ ሰራዊት ከሰዓት በኋላ ከአዘዞ ተነስቶ ገብቷል" ይላሉ።

በአካባቢው ሌላኛው ነዋሪ ግጭቱ ቀዝቀዝ እንዳለ ገልፆ የሟቾች ቀብርም ገንዳ ውሀ በሚባለው አካባቢም እየተከናወነ መሆኑን ይናገራል።

ሁለት ሟቾችም ደለሎ የሚባለው አካባቢ የተቀበሩ ሲሆን ሌላኛው ሟች ወደ ትውልድ ቦታው እንደተመለሰ እኚሁ ነዋሪ ገልፀዋል።

የሱዳን አርሶ አደሮችና የፀጥታ ኃይል እንደተገደሉ የዘገበው ሱዳን ትሪቢውን "እንዲህ አይነት ግጭቶች በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚከሰቱና የተጋነኑ ሊሆኑ እንደማይገባቸው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አልዳርዲሪ መሀመድን ጠቅሶ ዘግቧል።

ተያያዥ ርዕሶች