6 ሚሊዮን ብር፡ በማንዴላ እሥር ቤት ለማደር

ማንዴላ በታሰሩበት Image copyright AFP

ደቡብ አፍሪቃውያን ኔልሰን ማንዴላ ለነፃነት በሚታገሉበት ወቅት ታስረውበት በነበረው ክፍላቸው አንድ ሌሊት ያሳልፉ ዘንድ ዕድል ቀርቦላቸዋል።

በጨረታ መልክ የመጣው ዕድል ግን ጠረቅ ያለ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፤ ዝቅተኛው 250 ሺህ ዶላር፤ በብር ሲመነዘር ደግሞ ከ6 ሚሊዮን በላይ።

በሮበን ደሴት ላይ የሚገኘው ይህ እሥር ቤት የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ለ27 ዓመታት ታስረውበት የነበረ ነው።

ጨረታው 67 ሰዎችን የሚያካትት ሲሆን እኚህ ሰዎች ማንዴላ ባደሩባት ክፍል ለማደር በትንሹ 6.8 ሚሊዮን ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ጨረታው ለ12 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በኔልሰን ማንዴላ የውልደት ቀን ውጤቱ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከጨረታው የሚገኝ ገንዘብ ለታራሚዎች የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለሚያቀርብ አንድ ድርጅት እንደሚሰጥ የጨረታው አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል።

ማንዴላ ከእሥር የተለቀቁት በአውሮጳውያኑ 1990 ሲሆን ከአራት ዓመታት በኋላ በተደረገ ምርጫ በማሸነፍ የመጀመሪያ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል።

በበርካቶች ዘንድ የነፃነት አባት ተደርገው የሚቆጠሩትን ኔልሰን ማንዴላ የዛሬ 5 ዓመት ገደማ ነበር በ95 ዓመታቸው ይህችን ዓለም የተሰናበቱት።

ተያያዥ ርዕሶች