በደቡብ አፍሪቃ አውራሪስ አዳኞቹ በአንበሳ ተበሉ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእንስሳት ማቆያ ውስጥ ዘልቀው በመግባት አውራሪስ በማደን ላይ የነበሩ ግለሰቦች በአንበሶች ተበልተዋል። Image copyright SIBUYA GAME RESERVE

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእንስሳት ማቆያ ውስጥ ዘልቀው በመግባት አውራሪስ በማደን ላይ የነበሩ ግለሰቦች በአንበሶች ተበልተዋል።

አንበሶቹ ቢያንስ ሁለት አዳኞችን 'ውጠው አላየሁም' ማለታቸው እየተዘገበ ሲሆን የማቆያው ሰዎች ግን አዳኞቹ ሶስት ሳይሆኑ አልቀሩም ሲሉ ይገምታሉ።

የሁለቱ ሰዎች ቅሪት የተገኘ ሲሆን ለአደን ይረዳቸው ዘንድ ይዘውት የነበረ መሣሪያና መጥረቢያም ተገኝቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪቃ ውስጥ የአውራሪስ አደን እየበረታ የመጣ ሲሆን ለዚህ ደሞ እንደምክንያት እየተጠቀሰ ያለው በውድ ዋጋ ለገበያ የሚቀርበው የአውራሪስ ቀንድ ነው።

አውራሪስ በብዛት ከሚገኝባቸው የአፍሪቃ ሃገራት አልፎ ቻይና እና ቪየትናምን የመሳሰሉ ሃገራት በኢህ ጉዳይ ማጣፊያው አጥሯቸዋል።

የእንስሳት ማቆያ ሥፍራው ባለቤት የሆኑ ግለሰብ በፌስቡክ ገፃቸው አዳኞቹ ወደ ቅጥር ግቢው የገቡት ድቅድቅ ጨለማን ተገን አድርገው እንደሆነ አሰውቀዋል።

ግለሰቡ ጨምረው ሲገልፁ «አዳኞቹን አንክት አድርገው የበሏቸው አንበሶቹ በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ባናውቅም በርከት እንደሚሉ ግን እንገምታለን» ብለዋል።

የሰዎቹ ቅሪት ከተገኘ በኋላ ሁኔታውን ማጣራት ይረዳ ዘንድ አንበሶቹ ራሳቸውን እንዲስቱ ተደርጓል።

ፖሊስ ሌላ በአንበሳ የተበላ አዳኝ ይኖር እንደሆን ለማጣራት አካባቢውን ቢያስስም ፍንጭ ሊገኝ አልቻለም።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ አዳኞች በዚህ ማቆያ ሥፋራ የሚገኙ ዘጠኝ አውራሪሶችን መግደላቸው ተመዝግቧል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ብቻ ደግሞ 7 ሺህ ያህል አውራሪሶች የአዳኞች ሲሳይ ሆነዋል።