ቢጫና ቀይ ካርዶችን ማንና ለምን ፈጠራቸው?

ቢጫ ካርድ Image copyright Getty Images

አንዳንድ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በጣም ትግል የበዛባቸው ከመሆናቸው የተነሳ የጦር አውድማ መሆን ይቃጣቸዋል፤ ማረጋጊያ መንገድ እስኪጠፋ ድረስ። ፖሊስ ገብቶ የገላገላቸው በርካታ ጨዋታዎች መኖራቸውን ልብ ይሏል። ይህን የተመለከተው ሰው ያመጣው ዘዴ እስከዛሬ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

«መኪናዬን እያሽከረከርኩ አንድ መንገድ ላይ የትራፊክ መብራት ያዘኝ፤ ቁጭ ብዬ አሰላስል ያዝኩ። ቢጫ ተጠንቀቅ ነው ቀይ ደግሞ ቁም።»

ይህች ቅፅበት እግር ኳስን የቀየረች ሆና ተመዘገበች። እንግሊዛዊው አርቢትር ኬኔት ጆርጅ አስተን ይህን ዘዴ ለምን እግር ኳስ ላይ አይተገበርም የሚል ሃሳብ ብልጭ አለለት።

ጊዜው በፈረንጆቹ 1960ዎቹ ገደማ፤ 'ኧረ በሕግ' ባይ ያጡ የሁለት እግር ኳስ ቡድን አባላት ቡጢ ገጠሙ፤ ሜዳው የፀብ አውድማ ሆነ። የተጎዱ ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ።

ይህ የሆነው በፈረንጆቹ 1960 ላይ በቺሊ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ነበር።

የሳንቲያጎ አውድማ

በመክፈቻው ጨዋታ ሶቪየት ሕብረትና ዩጎዝላቪያ ጨዋታ ገጠሙ፤ ኧረ ቡጢ ገጠሙ ማለት ይቀላል።

ጀርመን እና ጣልያን ያደረጉት ጨዋታም እንዲሁ መፈነካከት የተሞላ ነበር። አጥንቶች ተሰበሩ፤ የአርቢትሩም ፊሽካ የሚሰማ ጠፋ።

'እስቲ ዛሬ እንኳን ሰላማዊ ጨዋታ እንይ' ብለው ሦስተኛውን ቀን የጠበቁ ተመልካቾች በቼኮዝሎቫኪያ እና በስፔን መካከል የተደረገውን ግጥሚያ. . . ይቅርታ. . .ፍልሚያ ሊያዩ ግድ ሆነ፤ አንዳንድ ተጫዋቾች ቡጢው ራሳቸውን አሳታቸው።

አርጀንቲናና ቡልጋሪያም እንዲሁ ሜዳውን ወደ የግብግብ አውድማነት ቀየሩት።

Image copyright Getty Images

'መች ተለካካንና' ያሉ የሚመስሉት የጣልያንና የቺሊ ብሔራዊ ቡደኖች ታሪክ ፃፉ፤ የሳንቲያጎ አውድማ ተብሎ የሚጠራውን ታሪክ።

ቡጢ፣ ካራቴ፣ ጥፊ . . . ብቻ ጨዋታው ደንበኛ በድርጊት የተሞላ (Action) ሲኒማ ሆኖ አረፈው።

ጨዋታው በቺሊ 2 ለምንም አሸናፊነት ተቋጨ። አርቢትሩ ግን ከትችት አልተረፉም፤ ኧረ ቡጠም ቀምሰዋል።

ዳኛው እንግሊዛዊው ኬኔት ጆርጅ አስተን ነበሩ፤ የቢጫና ቀይ ካርድ ሃሳብ ብልጭ ያለላቸው ግለሰብ።

ጊዜው በፈረንጆቹ 1970 ዓ.ም፤ የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ። አርቢትር አስተን 'ግድ የላችሁም አንዲት ሃሳብ አለኝ፤ አድምጡኝ' ሲሉ ተሰሙ።

«እኔኮ የእግር ኳስ ዳኝነት ሳይሆን በሁለት ቦክሰኛ መካከል ያለ አቧቃሽ ነበርኩ» ክስተቱን እንዲህ ነበር የዘከሩት።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኬኔት አስተን

22 ተዋናዮች የሚሳተፉበት ደንበኛ ሲኒማ

አርቢትሩ 1963 ላይ 'አሁንስ በቃኝ ባይሆን ከሜዳ ውጭ ባለው ላግዛችሁ' ብለው የፊፋ ዳኞች ኮሚቴን ተቀላቀሉ።

ኮሚቴውን በፕሬዝደንትነት መምራት ዕድሉን ያገኙት አስተን 1966 ላይ ሃገራቸው እንግሊዝ ከአርጀንቲና ስትጫወት የተፈጠረው ነገር ሰቅዞ ያዛቸው።

የዕለቱ አርቢትር ጀርመናዊው ሩዶልፍ ነበሩ፤ ጥፋት ፈፅሟል ያሉትን የአርጀነቲና አምበል ከሜዳ እንዲወጣ አዘዙ፤ አምበሉ ግን አሻፈረኝ አለ።

ችግሩ የነበረው ዳኛው ሰፓኒሽ አለመቻላቸው፤ ተጫዋቹ ደግሞ ጆሮው ቢቆረጥ ጀርመንኛም ሆነ እንግሊዝኛ አለመቻሉ ነው።

አስተርጓሚ እስኪመጣ በሚል ለ10 ደቂቃ ያህል ጨዋታው ተቋረጠ። ትርጉሙን የሰሙ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ግን 'ፍንክች የአባቢላዋ ልጅ'።

ሁኔታው ያልጣማቸው የእንግሊዝ ፖሊሶች ዳኛው ከበው ከሜዳ አሸሿቸው።

የጊዜው የዳኞች ኮሚቴ አለቃ አስተን ወደሜዳ ገብተው ሁኔታውን ካረጋጉ በኋላ ጨዋታው እንዲቋረጥ ሆነ።

ይሄኔ ነው ሰውዬው ለዚህ ጉዳይ መላ መዘየድ ግድ ሆኖ የታያቸው፤ የትራፊክ መብራቱ ሃሳብም እውን እንዲሆን መንገድ ተጠረገ።

«እግር ኳስ 22 ተዋናዮች የሚሣተፉበት ዳኛው ደግሞ እንደ አዘጋጅ ሆኖ ማገልገል ያለበት መድረክ ነው» ሲሉ ነበር አርቢትሩ ስለኳስ ያላቸውን እምነት ያንፀባረቁት።

«ስክሪፕት የሌለው፣ መጀመሪያውም መደምደሚያውም ወረቀት ላይ ያልሰፈረ ትዕይንት ሊሆን ይገባል፤ ፍርደ ገምድልነት ግን ሊንፀባረቅበት የማይገባ» ሲሉ አስረግጠዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ