ልዩ መሰናዶ ካለሁበት 39፡ ሎስ አንጀለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 100 ቀናት ውስጥና በፊት

ብርሃኑ አስፋው በምግብ ቤታቸው Image copyright BERHANU ASFAW

ብርሃኑ አስፋው እባላለሁ ኑሮዬን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ ከተማ ካደረኩኝ ዘመናት ተቆጠሩ።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀኩኝ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እንድቀጥል ስፖንሰር ወይም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግልኝ አግኝቼ ነበር ወደአሜሪካ የመጣሁት።

በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወርኩ የማየትና የመኖር እድል ቢኖረኝም እንደ ሎስ አንጀለስ የሚሆንልኝ ግን አላገኘሁም። ስለዚህ ሥራ ፈልጌ ከተረጋጋሁ በኋላ ቤተሰቤን አምጥቼ ኑሮዬን ሎስ አንጀለስ አደረኩ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት

ካሊፎርኒያ ውስጥ ወደ 200 ከተማዎች አሉ፤ ከእነርሱም መካከል ብዙዎቹ አንዳንድ የኢትዮጵያን ገጽታዎች ያስታውሱኛል።

ከአየሩ ፀባይ እስከ መልከዓ ምድሩ፤ የካሊፎርኒያ ተራራማነትና ሌሎችም ነገሮች ወደ ኢትዮጵያ ይመልሱኛል።

የሳን በርናርዲኖ ካውንቲ አንዳንድ ቦታዎች የድሬዳዋ ከተማን በጣም ያስተውሰኛል።

ክረምት ላይም እንደ ሃገር ቤት ዝናባማ አይሁን እንጂ ብዙ ነገሮች ይመሳሰሉብኛል።

እንደዚያም ሆኖ ግን በተለይ ድሮ ወደ ሎስ አንጀለስ አየር ማረፊያ አካባቢ በማቀናበት ጊዜ ኢትዮጵያ ሳለሁ በመርካቶ ዙሪያ እመላለስ ስለነበር እዚያው የተመለስኩ ያህል ይሰማኝ ነበር።

ከሁሉም በላይ ግን 'ሊትል ኢትዮጵያ' ማለትም 'ትንሿ ኢትዮጵያ' የተሰኘው መንገድ ምን ጊዜም በቅፅበት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የመጣሁ ያህል እንዲሰማኝ ያደርጋል።

Image copyright BERHANU ASFAW
አጭር የምስል መግለጫ መሶብ የተሰኘው የብርሃኑ ምግብ ቤት፣ በ'ሊትል ኢትዮጵያ'

ኢትዮጵያን በትንሹ በሎስ አንጀለስ

የታክሲ ሹፌሩ፣ ዶክተሩ፣ ኢንጂነሩ እንዲሁም የምግብ ቤት ባለቤቱና አስተናጋጁ ሁሉ በሎስ አንጀለስ እቅፍ ውስጥ ይገኛል።

በሎስ አንጀለስ 'ሊትል ኢትዮጵያ' የተሰኘው መንገድ የተሰየመው እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም ነው።

እዚህ ሎስ አንጀለስ ኢትዮጵያውያን መልከ ብዙ መሆናችን ብቻ ሳይሆን ተራርቀን ስለምንኖር ማህበራዊ ኑሮዋችን ዋሺንግተንና ኒው ዮርክ እንዳሉት አይደለም።

ድምፃችን በሃገራችን የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ እምብዛም አይሰማምም ነበር።

በአንድ ወቅት ለአንድ ግለሰብ እርዳታ ለማበርከት አራት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተሰባስበው አብሬያቸው እንድሳተፍ ጠየቁኝ። ከዚያ በኋላ የተሳትፏችን መልክ ተቀየረ።

በጊዜው ዛሬ 'ሊትል ኢትዮጵያ' በተባለችው ሰፈር ውስጥ ነባር ባህላዊ ምግብ ቤቶችም ይገኙበት ስለነበር፤ መንገዱን በስማችን ለማስጠራት ቅስቀሳ አድርገን ፈቃድ ልናገኝ ችለናል።

ይህን ካቋቋምን በኋላ በዚያው ዓመት እኔም መንገዱ አቅራቢያ የነበረች አንድ ምግብ ቤት ከወንድሜ ጋር ከገዛን በኋላ ሥራ ጀመርን፤ ይኸው አሁን 18 ዓመት ሆኖናል።

በተጨማሪም የ'ሊትል ኢትዮጵያ የንግድ ማህበር' ፕሬዝዳንት ሆኜ ለ15 ዓመታትም አገልግያለሁ።

የመንገዱ ስያሜ ከተፈቀደልን ወዲህ የባህላዊ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ ባህላዊ ምግብ ቤቶችና የልብስ መደብሮች ተከፍተውበታል። በመንገዱ ጫፍና ጫፍም ላይ በሰማያዊ ታፔላ 'ሊትል ኢትዮጵያ' የሚልና የሐረር ጀጎል፣ የቡና፣ የጎንደር ቤተ መንግሥትና አክሱምን የሚያንፀባርቁም ባነሮች ተሰቅለውልናል።

በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ውጭ መንገድ የተሰየመለት ሌላ አፍሪካዊ ሃገር ስለሌለና እኛ ብቸኛዎቹ በመሆናችን እኮራለሁ። ከዚያም በላይ በጣም እንድኮራ የሚያደርገኝ ግን በምግብ ቤቴ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የተለያየ ሃገር ዜጎችን ማስተናገድ መቻሌ ነው።

ኤርትራውያን በተለይ በጣም ደንበኞቼ ናቸው። ለጥምቀት፣ ለምርቃት፣ ለመልስና ለመሳሰሉት ማህበራዊ ስብሰባዎች የምግብ ቤቴን አዳራሽ በተደጋጋሚ ይከራያሉ። በምግብም ሆነ በባህላችን በጣም ስለምንቀራረብ 'መሶብ' ለእነርሱም ቤታቸው ነው።

ይህንን መንገድ በይበልጥ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ማንኛውም ከአፍሪካ ጋር የተገናኘ ነገር ሲከሰት ዋና ቦታ መሆኑ ነው። ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ትራምፕ በተመረጡበት ጊዜ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የአፍሪካውያንን አስተያየት ለመቀበል ካሜራዎቻቸውን በ'ሊትል ኢትዮጵያ' ነበር ይዘው የመጡት።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ ሰልፍ መውጣት ቢፈለግ እንኳን በዚሁ መንገድ ላይ ነው ሰው የሚሰባሰበው። ለዚህም ነው ለኢትዮጵያውን በተለይ ይህች መንገድ በጣም ትልቅ ቦታ ያላት። መንገዱንም ለአዲስ ዓመት መዝጋት ተፈቅዶልን ድንኳን ጥለን ተሰብስበን ስንደገስ አሁን 16 ዓመታት አስቆጥረናል።

Image copyright BERHANU ASFAW
አጭር የምስል መግለጫ ኢትዮጵያውያን በ'ሊትል ኢትዮጵያ' አውራ ጎዳና ተሰብስበው

ከክፍፍል ወደ ጥምረት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ በጣም እየገረመኝ የመጣው በሎስ አንጀለስ ያሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ጎራ እየለዩ ይመገቡባቸው የነበሩ ምግብ ቤቶች የነበረ ሲሆን አሁን ግን መንፈሳቸውና ስሜታቸው የታደሰ ይመስል መከፋፈሉን እንደተዉ ማየቴ ነው።

ለምሳሌ አልፎ አለፎ የኤምባሲ ሰዎች በሚጠቀሙበት ምግብ ቤት ውስጥ ለመመገብ ፈቃደኛ ያልሆኑና አቋማቸው ከረር ያለ ሰዎች አይጠፉም ነበር፤ አሁን ግን በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ እንኳን መሻሻል ይታያል።

ኢትዮጵያዊያን የጎሪጥ መተያየት ትተን መቀራረብና መፋቀራችንን ሳይ ልቤ በደስታ ይሞላል።

ከዚህ ቀደም ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት መላክ የለበትም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሁን በሙሉ ደስታ ወደ ሃገር የመመለስ ሃሳብ ሁሉ እያውጠነጠኑ ሳይ ልቤን ይሞቀዋል።

የአንድነት ስሜቱ በይበልጥ የሚጎላው በኢትዮጵያም በካሊፎርኒያም ያለው ስሜት ተመሳሳይ መሆኑ ነው።

በዚህ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ጥሩና የሚያስደስቱ ለውጦች እያሳዩን በመሆናቸው በሎስ አንጀለስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙሉ በሙሉ የዶ/ር ዐብይ ደጋፊዎች ይሆናሉ ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ።

Image copyright BERHANU ASFAW
አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ወደ ቀኝ ፡ ብርሃኑና ወንድሙ ሽልማት ሲረከቡ፣ ብርሃኑና ወንድሙ ሽልማቱን በምግብ ቤታቸው ከመስቀላቸው በፊት፣ ሽልማቱ

አዲስና ሎስ አንጀለስ ምንና ምን ናቸው?

ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ አንፃር ወንጀል እስካልተሠራ ድረስ የማንኛውም ሰው መብት የተጠበቀ በመሆኑ ከሃገር ቤት ለየት ያደርገዋል።

በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ሰው ሊያገኝ ይገባዋል ተብሎ የሚታሰበውን ነገር በሙሉ ያለምንም ችግር ለሁሉም እኩል ይቀርባሉ፤ በዚህ በዚህ ሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያ ትለያለች።

ዛሬ ከአካባቢያችን አልፎ፣ ማህበረሰባችንን ማቆራኘት ከዚያም አልፎ በከተማው እውቅና እስከማግኘት በመድረሴ ይህች ሃገር ለሠራተኛና ለትጉህ ሰው በጎ መሆኗን በሙሉ አፌ መመስከር እችላለሁ።

ከእንጀራ ውጪ የሉዊዚያና ጋምቦ የተሰኘውን ከአሜሪካ ደቡብ ግዛቶች አካባቢ የተለመደውን ምግብ በጣም እወደዋለሁ። እንዲሁ ሳስበው የወደድኩት ስለሚያቃጥልና እንደ ወጥ ያለ ስለሆነ ይመስለኛል። ምንም ቢሆን ግን እንደ እንጀራ የሚሆንልኝ ምግብ የለም።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሉዊዚያና ጋምቦ

የወደፊት ምኞቴ በጣም ሰፊ ባይሆንም እንኳን ለሃገሬ ሰላምና ተስፋን እመኛለሁ። አሁን ደግሞ ሃገሪቱ የተያያዘችው መንገድ በጣም አስደሳች ነው። ሁሌም እመኘው የነበረው የኢትዮጵያዊው ማህበረሰብ ተጠናክሮና ባህሉንም ሆነ አንድነቱን ይዞ እንዲቀጥል ነው። በተለይ ወጣቱ ከወላጅና ከዘመዱ ጫና ውጪ በእራሱ ተነሳሽነት ወደ ባህሉ ሲመለስ ማየት ሕልሜ ነው።

ኢትዮጵያ በየተወሰነ ጊዜ እመላለሳለሁ፤ መሬት ገዝቼም ሥራ ለመጀመር አስቤ ነበር ግን ሳይሳካ ቀርቶ ትቼው የነበረ ቢሆንም አሁን በተለይ ቢቻለኝ ሐዋሳ ላይ ሥራ ብጀምር ደስታዬ ነው።

ብዙ ከተማዎችን አይቼ ሳይሆን እስካሁን ካየኋቸው ከተሞች መካከል ሐዋሳ በጣም ስባኝ ነበር። በተለይ የሰዉ ባህሪ፣ ሰው ወዳጅነታቸውና ከተለያየ ብሔርና ማህበረሰብ የመጡ ቢሆኑም በአንድ ላይ መኖራቸውን በጣም ወድጄላቸዋለሁ።

ስለዚህ እራሴን በቅፅበት ከሎስ አንጀለስ ኢትዮጵያ ብወስደው ሐዋሳ ሐይቅ ዳር ብገኝ እመኛለሁ።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 40: "ካለ ቪዛ ወደ 127 አገራት መጓዝ እችላለሁ"

ካለሁበት 41: ከባሌ እስከ ቻድ የተደረገ የነጻነት ተጋድሎ

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ