ትዊተር 70 ሚሊዮን ሃሰተኛ ገጾችን ዘጋ

የትዊተር አርማ Image copyright Reuters

ትዊተር ማንነታቸው የማይታወቁ፤ አጠራጣሪ መረጃዎችን ከተለያዩ ቦታዎች የሚያሰራጩና ትዊተርን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ናቸው ያላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትዊተር ገጾችን ዘጋ።

ትዊተር ከባለፈው ግንቦት ወዲህ ብቻ በውሸት የተከፈቱና አጠራጣሪ ናቸው ያላቸውን 70 ሚሊዮን የሚሆኑ ገጾችን መዝጋቱን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አስታውቋል። ይህ ገጾቹን የመዝጋትና የማገድ እንቅስቃሴ ድርጅቱ ለተጠቃሚዎች ምቹ ሁነታዎችን ለመፍጠርና ተአማኒነቱን ለመጨመር እንደሆነ ተገልጿል።

አብዛኛዎቹ ገጾች ማንነታቸው የማይታወቁ፤ አጠራጣሪ መረጃዎችን ከተለያዩ ቦታዎች የሚያሰራጩና ትዊተርን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ናቸው። ትዊተር በበኩሉ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ ላይ ለመጨመር ባይፈልግም ትልቅ የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ግን ገልጿል።

የትዊተር የደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት ዴል ሃርቪ ለጋዜጣው ሲናገሩ ድርጅቱ የተጠቃሚዎቹን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ ሁሉም ሰው በነጻነት የመሰለውን እንዲናገር ሲያደርግ እንደነበር ገልጸዋል።

አሁን በትልቁ ለመቀየር እተንቀሳቀስን ያለነው ነገር ሰዎች በነጻነት ሃሳባቸውን ሲገልጹ እንዴት የማንንም ስሜት በማይጎዳና አላስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን እንዳያስተላለፉ ማድረግ ላይ ነው በማለት አክለዋል።

በሌላ በኩል የድርጅቱ ቃል አቀባይ የሆኑ ሰው ደግሞ ዋሽንግተን ፖስት ይዞት የወጣው መረጃ አዲስ ነገር እንዳልሆነና አጠራጣሪ ገጾችን የመዝጋቱ ሂደት ትዊተር ለተጠቃሚዎቹ ምቹና ጤናማ የግንኙነት መስመር ለመፍጠር እያደረገው ያለው ስራ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ትዊተር 130 ሚሊዮን ደረጃቸውን ያልጠበቁና አጠራጣሪ መልእክቶችን ወደ ትዊተር ያስተላለፉ 142 ሺ የሚሆኑ መተግበሪያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ቃል አቀባዩ ጨምረዋል።

ትዊተር በአለማቀፍ ገበያ ያለው ድርሻ 8.5 በመቶ መቀነሱ ዋሽንግተን ፖስት ይህንን ዘገባ ይዞት ከወጣ በኋላ መሆኑ እየተዘገበ ነው። ምክንያቱም ይህን ያክል ቁጥር ያለው ተጠቃሚ (70 ሚሊዮን) የውሸት ከሆነ የማስታወቂያ ገቢው ላይ ከፍተኛ መቀነስ ሊያሳይ እንደሚችል ተገምቶ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ