ታንዛኒያ ቦይንግ "787-8 ድሪምላይነር" ገዛች

ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር Image copyright aviation-images.com

የታንዛኒያ አየር መንገድ በታሪኩ የመጀመርያ የሆነውን "787-8 ድሪምላይነር" ዘመናዊ አውሮፕላን ገዛች።

በዳሬሰላም የርክክርብ ሥነ ሥርዓት ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ እንደተናገሩት ታንዛኒያ በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ ቦታ እንዲኖራት ትፈልጋለች።

"በአሁኑ ጊዜ ትልቅ የአቪየሽን አገልግሎት የማይፈልግ አገር የለም" ያሉት ማጉፉሊ ታንዛኒያዊያን የንግድ ትስስር ከተቀረው ዓለም ጋር ለመፍጠር አቪየሽኑን ማሳደግ እንደሚያስፈግ አውስተዋል።

262 መቀመጫዎች ያሉትን ይህን ድሪምላይነር አውሮፕላን "ኪሊማንጃሮ" ስትል በአገሪቱና በአህጉሪቱ ትልቁን የተራራ ስም ሰጥታዋለች።

በመጪው መስከረም ወደ ሙምባይ፣ ጓንዡ እና ባንኮክ በመብረር ሥራ እንደሚጀምር ታውቋል።

ይህ አውሮፕላን የታንዛኒያ መንግሥት በኪሳራ ቋፍ ላይ የሚገኘውን የአቪየሽን ኢንደስትሪ ለመታደግ የሚያደርገው 4ኛው የአውሮፕላን ግዢ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነርን 787-8 ለመረከብ በአፍሪካ የመጀመርያ ሲሆን አውሮፕላኑንም የተረከበው ከአምስት ዓመታት በፊት በነሐሴ 2005 ነበር።