ከዋሻ የወጡት ሕጻናት ለአለም ዋንጫ ፍጻሜ ተጋበዙ

ህጻናቱን ከዋሻው ለማውጣት የተሰማሩት የባህር ሃይል አባላት

በዋሻ ውስጥ ለ17 ቀናት የቆዩት ሕጻናት ከዋሻው ሲወጡ በጉጉትና በጭንቀት ሲጠብቋቸው የነበሩ ቤተሰቦቻቸውና ሌሎች ታይላንዳውያን በአስገራሚ ደስታ ተቀብላዋቸዋል። የታይላንድ የባሕር ኃይል አባላት እልህ አስጨራሽ የሆነ ልጆቹን የማዳን ሥራቸውን ከቀናት በፊት ቢጀምሩም ሁሉንም ግን በአንድ ጊዜ ማውጣት አልቻሉም ነበር። ትላንት ምሽት ከዋሻው የወጡት አምስት ሕጻናት የመጨረሻዎቹ ናቸው።

የባሕር ኃይል አባላቱ ሕጻናቱን ከዋሻው ወደ ውጪ ለማውጣት ሦስት ፈታኝ ቀናት የፈጀባቸው ሲሆን፤ ይህ አሳዛኙ ሁኔታ የመላውን ዓለም ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። 12ቱም ሕጻናት ከነአሰልጣኛቸው በሰላም ሲወጡ የተመለከቱ ታይላንዳውያንና መላው ዓለም ደስታውን እየገለጸ ይገኛል።

በታይላንዷ ቺያንግ ራይ አውራጃ ሰኔ 15 ሕጻናቱና የእግር ኳስ አሰልጣኛቸው የታም ሉአንግ ዋሻን ሲያቋርጡ በድንገት ባጋጠመ የዝናብ ጎርፍ መንገድ ተዘግቶባቸው ነበር የሰነበቱት። በዚህ ክስተት ታግተው ቀሩትን 12 ሕጻናትና አሰልጣኛቸውን በሕይወት ለማዳን ከ12 በላይ የባሕር ኃይል አባላት የተሳተፉ ሲሆን፤ ትላንት ምሽት የነፍስ ማዳን ሂደቱ ያለ ምንም ችግር ፍጻሜውን አግኝቷል።

ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 17 የሆኑት እኒህ ሕጻናት ዋይልድ ቦርስ የተባለ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ሲሆኑ፤ በወቅቱ ከአሰልጣኛቸው ጋር በመሆን ዘና ለማለት ነበር ወደ ዋሻው የተጓዙት።

ሁኔታውን በቅርበት ስከታተለው ነበር ያለው የዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ''ፊፋ'' 12ቱን ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በመጪው እሑድ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ እንዲመለከቱ ጋብዟቸዋል።

እንደ ማንቸስተር ዩናይትድና ቤነፊካ ያሉ ክለቦች ደግሞ የስልጠናና የእግር ኳስ ትጥቅ እርዳታ እንደሚያደርጉላቸው ቃል ገብተዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑ አባላትና አሰልጣኛቸው ዋሻው ውስጥ መቅረታቸውን ማንም አላወቀም ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው የውሃ ጠላቂዎች ሁኔታውን ተመልክተው ለሚመለከታቸው የታይላንድ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

በዋሻው ውስጥ ለቀናት በመቆየታቸው የተዳከሙትን ሕጻናትና አሰልጣኛቸውን የማዳን ሥራው የውሃ ዋና አለመቻላቸው ደግሞ ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎት ነበር።

ውስብስ የነበረው የእግር ኳስ ቡድኑን አባላት የማዳን ሥራው፤ ባለፈው ዕሑድ ነበር አራት ሕጻናትን ከዋሻው በማውጣት የተጀመረው። በቀጣዩ ቀን ደግሞ ሌሎች 4 ሕጻናትን ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ ማክሰኞ ምሽት የመጨረሻዎቹን 4 ሕጻናትና አሰልጣኛቸውን በሰላም ማውጣት ተችሏል።

የሕይወት አድን ሥራውን በዋነኛነቱ ሲሠራው የነበረው የታይላንድ የባሕር ኃይል ተአምር ይሁን ሳይንስ፤ ብቻ 12ቱንም ሕጻናት ከነአሰልጣኛቸው ያለምንም ጉዳት ማዳን ችለናል ብሏል። በአሁኑ ሰአት ከዋሻው የወጡት የቡድኑ አባላት በሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።

በዋሻው ውስጥ በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት ሕጻናቱ የክብደት መቀነስ የታየባቸው ሲሆን፤ ጨለማ ውስጥ ለረጅም ቀናት ስለቆዩ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ዕይታቸው በመነጽር እንዲታገዝ ግድ ብሏል።