ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር የጀመሩትን የአብሮነት እርምጃ ምን ይፈትነዋል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (በስተግራ) ከኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ስምምነት ሲፈራረሙ

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለት አሰርት አመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ ሰፍኖ የዘለቀዉን ሞት አልባ ጦርነት ለመቋጨት የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ካሳወቀ ከ18 ቀናት በኋላ የኤርትራ መንግስት ጥሪውን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ማሳወቁ ይታወሳል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የተመራውን የልኡካን ቡድን እራት በጋበዙበት ምሽት ባለፉት 25 አመታት የተፈጠሩ ሰላም የማስፈን እድሎች በሁለቱ አገራት መሪዎች እምቢተኝነት ምክንያት ለፍሬ አለመብቃታቸውን ገልፀው ያለፈው ጊዜ እንዳይደገም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አብረው ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው "የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዳናረጋግጥ የተጋረጠብንን የመለያየት ግድግዳ አፍርሰን፣ ላለፉት 20 አመታት ከባድ ኪሳራ ያደረሰብንን ሞት አልባ ጦርነት ቋጭተን፣ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የጀመርነዉ ጉዞ እንደሚሳካ አልጠራጠርም" ብለዋል።

ከ1998 ዓ. ም. ጀምሮ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ተቋርጦ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአገራቱ መንግስታት ለሰላም ያሳዩት ተነሳሽነት ለሁለቱ አገራት እንዲሁም ለቀጠናውም ሰላምና ልማት መንገድ እንደሚከፍት በርካቶች ይስማሙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የሁለቱ አገራት ሰላም ለቀጠናዉ መረጋጋትና ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዚህ ትውልድ 'አለመግባባት' የሚባል መሰናክል መኖር እንደሌለበት ተናግረዋል።

መሰረታዊ ግንኙነቶችን ያኮላሸ ጦርነት

በካናዳ ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ኤርትራዊ ዓወት ተወልደ ወልደሚካኤል (ዶ/ር) በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀከል የተካሄደዉ ጦርነት የማይተመንና የማይተካ የሰው ህይወትና አቅም እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም ማስከተሉን ይናገራሉ። ጦርነቱ በተለይም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱንም አገር ዜጎች ኪሳራ አሸክሟል ይላሉ።

"ጦርነቱ ካቆመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን 'ጦርነት በሌላ ስልት' ተብሎ የሚታወቀው ሞት አልባ ጦርነት መሰረታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን አኮላሽቷል" ሲሉ የጦርነቱን ጠባሳ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ታራምድ የነበረው የማዳከም ስትራቴጂና ኤርትራ ከቀጠናዉ ተሳትፎ ርቃ በሌላ የፖለቲካ አለም ዉስጥ መዋተትዋ፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እንዳይረጋጋ ምክንያት መሆኑን መምህሩ ያወሳሉ።

"ምስራቅ አፍሪካ ከኢትዮጵያና ኤርትራ ባሻገር ለአለም አገራትም በጣም ስትራቴጂያዊ ቀጠና ነው። ቀጠናው አሜሪካ ውስጥ ከደረሰዉ 9/11 የሽብር ጥቃት በኋላ የሽብር ተግባርን ለማጥፋት የተጀመረዉ ትግል ዋነኛ የቴአትር ቦታ ሆኗል። የሁለቱ ሀገራት አለመረጋጋት ሶማሊያን የሽብርተኞች መንደር እንድትሆን አድርጓታል" ይላሉ።

ኤርትራ ኢትዮጵያ ስትከተለዉ ከነበረዉ የማዳከም ስትራቴጂ ለመውጣትና የራስዋን ጥቅም ለማስከበር የወሰደችው እርምጃ የአረብ ሀገሮች ወታደራዊ መቀመጫ እንድትሆን አድርጓታል።

አሁን ሁለቱንም አገራት የከፈቱት የሰላም በር ላለፉት 20 አመታት የነበረውን ጦርነት የሸበበው ሸካራ ግንኙነት ከማደሱ ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል።

ዶክተር ዓወት ተቀራራቢ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ገጽታ ያላቸው የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተቀናጀ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል አቅም እንደሚገነቡ ያምናሉ።

ሁለቱንም አገራት በዚህ ቀጠና ትልቅ ሚና መጫወት የሚያስችል አቅም አላቸው። በጎረቤቶቻቸዉ በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን የታየውን ጦርነትና አለመረጋጋት እንዲያረግቡ ተጥሎባቸዉ የነበረው ተስፋ ዳግም እንደሚያንሰራራ መምህሩ ይናገራል።

ከዚህ ባሻገር ባለፉት ሦስት ወራት ኢትዮጵያ ዉስጥ የተስተዋሉ ለውጦች ኤርትራ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ለውጥ እንድታደርግ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እንደሚያስገድዱ ዶክተር ዓወት ይናገራሉ።

ሁለቱ አገራት በሰብአዊ መብትና ሁለገብ ለውጥ ረገድ ይነሱባቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጡ ያላቸውን ተስፋም ያክላሉ።

ተስፋ መሰል መሰናክሎች

ዶክተር ዓወት እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሰት የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ እንደሚተገብር መግለጹ የሚደነቅ እርምጃ ቢሆንም የማንነትና ህልውና ጥያቄ ያነገቡ የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ከውሳኔው በፊት መወያየት ነበረብን የሚል ጥያቄ ማንሳቸውን ቸል ማለት አይቻልም ።

"ሆኖም ግን ህዝብ ለውይይት የሚቀርበው ወይም የሚጠራዉ አሁን አይደለም" ይላሉ።

እንደ መምህሩ ገለጻ ህዝብ ሳይወያይ ከውሳኔ በመደረሱ ቅሬታ አለ። "ይሁን እንጂ ድሮም ህዝቡን ቢያወያዩት ኖሮ ጦርነቱም ባልተጀመረ ነበር" ብለው አንድ መንግስት አለም አቀፋዊ ስምምነት ሲፈርም ስምምነቱን ለመተግበር እንደሚገደድም ያስረዳሉ።

ሁለቱም አገራት ስምምነቱን ሲፈርሙ የየራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁ የማንነት ጥያቄዎች በማንሳት ውሳኔዉን እንዳያደናቅፉት የድንበር ጥያቄዎቻቸው ተፈትሸው ውሳኔ መሰጠቱን ያጣቅሳሉ።

ዶክተር ዓወት ስለወደፊቱ ሲጠየቁ "የወደፊት ግንኙነታችን በሰው ሰራሽ ድንበር መደናቀፍ የለበትም። የውስጥ አስተዳደራዊ ችግሮችን በመፍታት መፍትሄ ማበጀት ይቻላል" ይላሉ።

"ሁለቱ መንግስታት የጀመሩት የሰላም መንገድ መረጋጋትና ጥሞና ይሻል"

መምህሩ በሁለቱ አገሮች መካከል አለመተማመንና አለመግባባት አሁንም መኖሩን ይገልጻሉ። ሁለቱ አገራት በቅድሚያ ውስጣዊ አስተዳደራዊ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዳለባቸውም ይጠቁማሉ።

"ሁለቱ መንግስታት የጀመሩት የሰላም መንገድ መረጋጋትና ጥሞና ይሻል" ሲሉም ሰከን ብሎ መጓዝን ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት አካሄድ የሰዎችን ስሜትና ፍላጎት እየኮረኮረ ሁኔታዎች የሚያንጸባርቅ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህን መሰረት በማድረግም ውሳኔዎች መዋቅራዊ ቅርጽ ይዘው በስርዓት መተግበር ካልጀሩ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም ይላሉ።

በተጨማሪም ሁለቱንም መንግስታት ድንበር ላይ ያላቸው ግጭት ለመፍታት ከመሯሯጣቸው አስቀድሞ የኤርትራ መንግስት የህዝቡን ጥያቄና ፍላጎት በማያሻማ መልኩ መመለስ መቻል አለበት ይላሉ።

መምህሩ በኤርትራ በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጡት "መንግስት ከባድ ዋጋ ተከፍሎበት የተኮላሸውን የኤርትራ ሰላም መመለስና የውስጥ ተቋማትን ማደራጀት አለበት" በማለት ነው።

ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ስምምነት ላይ ቢደርሱም ዘላቂ ሰላም ስለማይኖር ቆም ብሎ ማሰብ ያዋጣል ይላሉ።