«በረከት ስምዖን» አርፈውበታል የተባለ ሆቴል ጥቃት ደረሰበት

ደብረማርቆስ

የፎቶው ባለመብት, AT FACEBOOK

ዛሬ ረፋድ ላይ የተፈጠረ ግጭትን ተከትሎ በደብረ ማርቆስ ከተማ ውጥረት መንገሱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ''በከተማዋ በሚገኘው ጎዛምን ሆቴል 'አመራሮች በድብቅ እየተወያዩ ነው' በሚል የሀሰት ወሬ የተነሳሱ ወጣቶች በሆቴሉ ላይ ጥቃት በመክፈት ንብረት አውድመዋል። ይህንን ተከትሎ ደግሞ ከተማዋ ውጥረት ውስጥ መዋሏን ተናግረዋል።

ጠዋት ላይ የባጃጅ ሹፌሮዎች እና የትራፊክ ፖሊስ በባንዲራ አጠቃቀም እና በመሰል ጉዳዮች ላይ መጋጨታቸውን ተከትሎ የመንግሥት አካላት ሊያነጋግሯቸው ከሰዓት ቀጠሮ እንደነበራቸው የሚያስታውሱት የጎዛምን ሆቴል ባለቤት ዘመድ አቶ ሰለሞን ሽፈራው በበኩላቸው፤ በመካከል ግን ሆቴሉ ፊት ለፊት በሚገኘው የከተማዋ ደሴት የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት እንደተጀመረ ይናገራሉ።

«በመቀጠልም ሰልፈኞቹ 'በረከት (ስምዖን) ከሆቴሉ ይውጣ እያሉ ድምፃቸውን ማሰማት ቀጠሉ። የሆቴሉ አስተዳደር በሆቴሉ ውስጥ የተባሉት ባለስልጣን የሌሉ መሆኑን ከመናገር አልፈው ከሰልፈኞቹ መካከል የተወሰኑት ሆቴሉን ገብተው እንዲያዩ ቢያደርጉም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥቃት ተጀምሯል'' ብለዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ በመጀመሪያ ጥቃት የደረሰባት ከጀርባ የቆመች የጣና በለስ ፕሮጀክት ንብረት የሆነች መኪና ስትሆን በመቀጠል የሆቴሉን መስታወቶች የመስበር ድርጊት ተከትሏል። ከጎዛምን ሆቴል በተጨማሪ በአቅራቢያው ያሉ ሆቴሎች ጥቃት እንደተፈፀመባቸው፣ የከተማዋ ፖሊስ ሰልፈኞቹ ወደ ከተማው አስተዳደር አቅጣጫ እንዳይሄዱ ከመልከል ውጪ ንግድ ቤቶቹን ከጥቃት ለማዳን ያደረገው ጥረት አናሳ እንደሆነ ተናግረዋል።

የክልል ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዛሬው ክስተት ያጋጠመውን ጉዳት መጠን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ የገለፁ ሲሆን ይሄ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ የከተማዋ ውጥረት አለመብረዱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።